የህዳሴ ግድብ የመጀመሪየ ዙር የውኃ ሙሊት መጠናቀቅ ብሄራዊ ስኬት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ዘጠኝ አመታት መላው የሀገራችን ህዝቦች ለግድቡ ግንባታ ካላቸው ላይ ቆርሰው በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸው እና በእውቀታቸው የሚችሉትን እያደረጉ የግንባታውን ሂደት በጉጉት ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ ለግድቡ ከተደረገው ከፍተኛ ድጋፍ እና ጉጉት በተቃራኒ የግንባታው ሂደት በርካታ የቴክኒክ፣ የአስተዳደር እና ዲፕሎማሲያዊ ውጣ ውረዶች አጋጥመውታል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እነዚህን በርካታ ተግዳሮቶች አልፎ የመጀመሪያ ዙር የውሀ ሙሊት በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ መቻሉ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች እና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል፡፡ ግድቡ ውሀ ተሞልቶ በግድቡ አናት ላይ ሲፈስ ማየት በጉጉት ስንጠብቀው የነበረ እጅግ አስደሳች ክስተት ነበር፡፡

ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብቷ በተለይም በወንዞቿ መጠቀም ሳትችል በርካታ ትውልድ በድህነት እና በጨለማ አልፏል፡፡ በተለይ ታላቁን የአባይ ወንዝ ለሀገራችን እድገት እና ለኢትዮጵያውያን ህይወት መለወጥ ጥቅም ላይ ለማዋል መላው የሀገራችን ህዝቦች ለረዥም ዘመናት ሲናፍቁ ኖረዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የልማት እና የዳቦ ጥያቄ ነው፡፡ የዝናብ ጥገኛ የሆነው የሀገራችን ግብርና እንዲዘምን፣ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ፣ ከተሞቻችን እንዲያበሩ፣ በገጠር የሚኖሩ ወገኖቻችን ሸክም እንዲቀንስ፣ በማገዶ ሸክም የጎበጠው የእናቶቻችን ወገብ እንዲያገግም ሀገራችንን ወደተሻለ የእድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስፈልገንን ኃይል ለማገኘት የታላቁ ህዳሴ ግድብ በትልቅ ተስፋ እና በጉጉት የሚጠበቅ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ የግድቡ የውሀ ሙሊት ከድህነት በአጭር ጊዜ መውጣት ይቻላል የሚለው እምነታችን ይበልጥ እንዲጠነክር ተስፋችን እንዲያብብ አድርጎታል፡፡

ዛሬ ላይ የደረስንብት ስኬት የትላንት የጋራ ርብርብ ውጤት መሆኑ እሙን ነው፤ ከስኬት ሀዲድ ገባን እንጂ ጉዟችንን አላገባደድንም፡፡ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ጥቅም ላይ እስኪውል ብዙ ስራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል፡፡ ይህንን ውጥን እውን ለማድረግ ከምንም በላይ ሰላምና መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላማችንን ለመጠበቅ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በድርድር እና በመግባባት ለመፍታት በከፍተኛ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት ስሜት ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡

ለግድቡ ቀሪ ስራዎች ማጠናቀቂያ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ሀብት ማሰበሰብ ሌለው ትኩረት የሚሻ ስራ ነው፡፡ እንደ እስከ ዛሬው ሁሉ ድጋፍ በማድረግ እና ቦንድ በመግዛት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በደስታ ስናከብር ለግድቡ እውን መሆን በሀሳብ፣ በአመራር፣ በገንዘብ፣ በሙያ፣ በጉልበት፣ አስተዋጾ ላደረጉ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ ነው፡፡

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ያሳየነውን የትብብር መንፈስ አጠናክረን በመቀጠል ዜጎች በነጻነት እና በእኩልነት የሚኖሩባት ከድህነት እና -ፍትሀዊነት ነጻ ሀገር ለመገንባት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

እንኳን ደስ ያለን፡፡

 

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

ሀምሌ 15 2012

አዲስ አበባ

Comment:0