የኢኮኖሚ ፕሮግራም

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ከሚገኙ ድሀ ሀገራት አንዷ ስትሆን ግማሽ የሚጠጋው የሀገራችን ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ይኖራል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ስታትስቲካዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ሀገራችን ከአፍሪካ 7ኛ፣ ከዓለም 71ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ምጣኔ ሀብቷን በፍጥነት ለማሳደግ የሚያስችሏት ሰፊ እና ጥቅም ላይ ያልዋሉ የተፈጥሮ ሀብቶች በብዛት ያላት ሀገር ናት፡፡ የከርሰ ምድር ሀብቶች፣ ማዕድናት፣ ለግብርና ምቹ የአየር ንብረት፣ በርካታ ወንዞችና የከርሰ ምድር ውሀ፣ ወጣትና በአምራች እድሜ ላይ ያለ የሰው ኃይል ከብዙ በጥቂቱ ይገኙበታል፡፡ የግብርናው ዘርፍ የሀገራችን ኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ሲሆን ከፍተኛ የስራ ዕድል በመፍጠር እና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡

በሀገራችን የአገልግሎ ዘርፉ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ሲሆን ለአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ያለው ድርሻ ከግብርናው ዘርፍ በልጧል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና እና የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ያለው ድርሻ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በአንጻሩ የሀገራችን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአብዛኛው ጥሬ ሀብትንና የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር፣ በጨርቃጨርቅና በአግሮ ኢንደስትሪ ምርቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ዘርፉ ለሀገራችን ኢኮኖሚ የሚኖረውን አስተዋፅዖ ከፍ ለማድረግ ከግብርናና አገልግሎት ሰጭ ዘርፎች ጋር ያለውን ትስስር ማሳደግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ኢኮኖሚያችን ወደ ዘመናዊና ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ እንዲሸጋገር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሀገራችን ያሏትን ዕድሎችና መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም ዘላቂ፣ አረንጓዴ፣ በአፍሪካ እና በዓለም ተወዳዳሪ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የፓርቲያችን ዋና የኢኮኖሚ ዓላማ ሲሆን የሚከተሉት ዝርዝር ዓላማዎች አሉት፡፡

 1. ዜጎች ለኑሮ የሚያስፈልጓቸው መሰረታዊ ፍላጎቶች ተሟልተውላቸው የተረጋጋ እና ደስተኛ ኑሮ መኖር ይችሉ ዘንድ በቂ የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲኖራቸው ማስቻል፣
 2. አስከፊ ድህነትን መቀነስ ብሎም ማጥፋት፣
 3. በዜጎችና በክልሎች መካከል ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማስቻል፣
 4. ስራ አጥነትንና የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የረዥም ጊዜ አፍራሽ ተፅዕኖ ሊያደርስ የሚችል የኢኮኖሚ መዋዠቅን መከላከል እና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር፣
 5. የሀገራችንን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ታሳቢ ያደረገ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ሽግግር መፍጠር፣
 6. የኢኮኖሚ እድገትን ከአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ጋር በማቆራኘት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት፣

ስልቶች

ከላይ የተጠቀሱ ምጣኔ ሀብታዊ ዓላማዎችን እውን ለማድረግ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሚከተሉትን ስልቶች ይጠቀማል፡፡

 1. ኢንቨስትመንትን ቀላልና የተቀላጠፈ በማድረግ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች መዋዕለ-ንዋያቸውን በተቀላጠፈ መንገድ ስራ ላይ እንዲያውሉ ማድረግ፣
 2. ለኢኮኖሚ ልማት እንቅፋት እና አሳሪ የሆኑ ህጎችን በማስወገድ በምትካቸው ቀላል እና ለአተገባበር ምቹ ህጎችን ማውጣት፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት፣
 3. ፍትሀዊና ግልጽ የግብር ስርዓት መዘርጋት፣
 4. መንግስት ለዜጎችና ድርጅቶች ለኢኮኖሚ ልማት ጠቃሚ በሆኑ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ማበረታቻ መስጠት፣
 5. የተዝረከረከ እና የተጓተተ አሰራርን በማስቀረት በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ፣
 6. የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና ፕሮግራሞችን ከሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተናበቡ እንዲሆኑ ማድረግ፣
 7. የውጭ ብድርና እርዳታን መቀነስና አቅም በፈቀደ መጠን በራስ አቅም ላይ መወሰን፣
 8. የህዝብ ዕድገትን ከኢኮኖሚ ልማት ጋር እንዲጣጣም በማድረግ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣
 9. የፋይናንስ ዘርፉን የብድር ስርዓት አስተዳደር በማጠናከር የገንዘብና የኢኮኖሚ ቀውስን አስቀድሞ መከላከል፣
 10. ምጣኔ ሀብታዊ መረጃዎች በተፈለገበት ጊዜና ቦታ በቀላሉ እንዲገኙ ማስቻል፣
 11. ከጎረቤት ሀገሮችና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚና የንግድ ትስስር መፍጠር፣
 12. ግብርና፣ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎችን በማቀናጀት ምርትንና ምርታማነትን ማሳደግ፣
 13. ለባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ዋስትና መስጠት (Property right)፣
 14. የቁጠባ ባህልን በማዳበር ለኢንቨስትመንት በቂ ሀብት ከሀገር ውስጥ ማመንጨት የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር፡፡

የመንግስት ሚና

ነእፓ የኢኮኖሚ ዓላማዎቹን ለማሳካት በመሰረታዊነት ገበያ-መር የኢኮኖሚና የንግድ ስርአትን የሚከተል ሲሆን፣ የሀገሪቱን ልማት ለማፋጠንና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ የመንግስት ተሳትፎ አስፈላጊ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ኃላፊነት ይወጣል፡፡ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ እንዲሳተፍ የሚያስገድዱ ዋና ዋና ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ከፍተኛ የግንባታ መዋዕለ ንዋይ የሚፈልጉ እና ዝቅተኛ የትርፍ መጠን ያላቸው፣ ለግል ባለሀብቶች አዋጭ ወይም ሳቢ ያልሆኑ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መንግስት በብቸኝነት ወይም ከግሉ ዘርፍ ጋር በሽርክና ይገነባል፡፡ የየብስ እና የባቡር መንገዶች፣ ግድቦች፣ የሀይል ማመንጫ እና ማከፋፈያ አውታሮች፣ የትራንስፖርትና መገናኛ አውታሮች እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡
 2. በተሻለ ጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ለመስጠት ይቻል ዘንድ በአንድ አምራች ወይም አቅራቢ ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ በሚችሉ የአገልግሎት ዘርፎች መንግስት በብቸኝነት (Public Monopoly) ወይም ከግል ዘርፉ ጋር በጋራ ሊሰራ ይችላል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጾ ከፍተኛ ሲሆን ለሀገራችን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት (GDP) 35 ከመቶ በላይ እንዲሁም ለሀገሪቱ ህዝብ 70 ከመቶ በላይ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ ሀገራችን ወደ ውጭ ከምትልካቸው እቃዎች ከፍተኛው የግብርና ውጤቶች ሲሆኑ ዋናው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ ካለው ሀገራዊ ፋይዳ አንፃር ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሀገራችን ህዝብ በገጠር የሚኖር ሲሆን የገጠሩ የሀገራችን ክፍል ዝቅተኛ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች እና ደካማ የመሰረ-ልማት አቅርቦት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚና የገጠሩ የሀገራችን ክፍል ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነእፓ ከፍተኛ የፖሊሲ ትኩረት በመስጠት ከግብርናው ዘርፍና ከገጠር ልማት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡

ግብርና

 1. የሀገራችን የግብርና ዘርፍ ካለበት ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ እና የዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ወደ ተሻሻለ እና ሜካናይዝድ ግብርና እንዲቀየር ይደረጋል፣
 2. በመስኖ ላይ የተመሰረተ የእርሻ ስራ እንዲስፋፋ ለማድረግ ማበረታቻና ድጋፍ ይደረጋል፣
 3. የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለኢንዱስትሪና አገልግሎት ሰጪ ዘርፍ በቂ ግብዓት እንዲያቀርብና ለኢዱስትሪ ልማት ሰፊ ገበያ እንዲፈጥር የግብርናና የኢንዱስትሪ ሴክተሮች እንዲቀናጁ ይደረጋል፣
 4. የሀገራችን ኢኮኖሚ አሁን ካለበት የግብርና-መር ኢኮኖሚ በሂደት ወደ ኢንዱስትሪ-መር እንዲሸጋገር የሚያስችል መዋቅራዊ ሽግግር ይደረጋል፣
 5. የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በቂ ምግብ ማምረት እና ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችል ይደረጋል፣
 6. በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እስከ አሁን ድረስ ለእርሻና ለሌሎች የግብርና ስራዎች ያልዋሉ ለም መሬቶች ጥቅም ላይ እንዲዉሉ ይደረጋል፣
 7. ቡና፣ አበባ፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳን ጨምሮ ለሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የግብርና ምርቶች ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ይደረጋል፣
 8. ዘመናዊ የምርት መሳሪያዎችና የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከፍ እንዲል ይደረጋል፣
 9. ዘመናዊ የግብዓትና የምርት አቅርቦት ስርአትን በመገንባት የገበሬውን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ማሳደግ፣
 10. የሀገራችን ግብርና ዘርፍ ያለበትን የድህረ ምርት (Post harvest) ብክነት በመቀነስ የግብርና ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ ማድረግ፣
 11. ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ውጤቶች እና ጥሬ እቃዎች በሀገር ውስጥ እሴት ተጨምሮባቸው በተሻለ ዋጋ እና ጥራት ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ሀገራችን ከዘርፉ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እንዲያድግ ይደረጋል፣
 12. የግብርና ምርት እንዲቀንስ የሚያደርጉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘዴዎችና የተሻሻሉ የግብርና ግብዓቶች ስራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፣
 13. የግብርና-ኢንዱስትሪን (Agro-Industry) በማስፋፋት ገበሬው ምርቱን ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችልበት የገበያ ስርዓት ይዘረጋል፣
 14. የግብርናውን ዘርፍ አጠቃላይና ዝርዝር መረጃ በትክክል መሰብሰብ የሚያስችል የመረጃ ስርዓት በመዘርጋት ዘርፉ ያለበትን ደረጃ በየጊዜው ለማወቅና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ መቅረጽ የሚያስችል አሰራር ይዘረጋል፣
 15. ገበሬዎች ብድርና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን በቀላሉ የሚያገኙበት ስርዓት ተቀርጾ ተግባራዊ ይሆናል፣
 16. መሰረታዊ የምግብ አቅርቦትን በሀገር ውስጥ እንዲሸፈን በማድረግ ከውጭ ሀገር የሚደረግ የምግብ ግዥ እንዲቀንስ ብሎም እንዲቆም ይደረጋል፣
 17. በተወሰኑ የእህል እና የጥራጥሬ ዓይነቶች የተወሰነውን የአመጋገብ ባህል በመለወጥ በሀገራችን ውስጥ በቀላሉና በብዛት የሚመረቱ የእህል እና የሰብል ዓይነቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፣
 18. ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በተፈጥሮ ማዳበሪያ በመቀየር በአካባቢ እና በሰዎች ጤና ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል የተቀናጀ የግብርና፣ የምርምርና የግብይት ስርዓት ይዘረጋል፣
 19. የእንስሳትን ጤና በመንከባከብ የእንስሳት ምርትና የምርት ተዋፅዖ እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ ገበሬው ከእንስሳቱ የሚያገኘው ጥቅምና ገቢ እንዲያድግ ስልት ይቀየሳል፣
 20. ሰፋፊ/ትልልቅ የንግድ እርሻዎች /Large Scale Commercial Farming/ እንዲስፋፉና እንዲበረታቱ ይደረጋል፣
 21. የግብርናው ዘርፍ ዕድገት ለስራ ፈጠራና ለድህነት ቅነሳ ጉልህ ሚና እንዲኖረው ይደረጋል፡፡

የገጠር ልማት

ከሀገራችን ህዝብ አብዛኛው በገጠር የሚኖር ሲሆን፣ የገጠሩ የሀገራችን ክፍል ከከተሞች ጋር ሲነጻጸር በልማትና በአገልግሎት አሰጣጥ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፣

 1. በጥናት ላይ የተመሰረቱ የተቀናጀ የገጠር ልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 2. መልከዓ-ምድራዊና ስነ-ምህዳርን ታሳቢ ያደረጉ የገጠር ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ፕሮግራሞች ተቀርጸው በስራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፣
 3. ትምህርት፣ ጤና፣ መብራት፣ የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ የስልክ አገልግሎት የመሳሰሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በገጠር አካባቢ በጥራትና በብዛት እንዲቀርቡ ይደረጋል፣
 4. አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ግድቦችን በመገንባት ገበሬው የመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል፣
 5. የገጠሩን ኢኮኖሚ ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ የገጠር የስልጠና ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ በስፋት ይሰራል፣
 6. በገጠሩ አካባቢ አነስተኛና ወጪ ቆጣቢ ቤቶች በመገንባት የህብረተሰቡ ኑሮ እንዲሻሻል ይደረጋል፣
 7. ለገጠሩ ህብረተሰብ የስራ ዕድል በመፍጠር ድህነትን የሚቀንሱ ፕሮጀክቶች በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ተግባራዊ ይሆናሉ፣
 8. መንገድን ጨምሮ ሌሎች የገጠር መሰረተ-ልማቶችን በማስፋፋት ምርታማነትን የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ይቀየሳሉ፤ የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በርስና ከከተሞች ጋር የሚያገናኙ የገጠር መንገዶች እንዲገነቡ ይደረጋል፣

ከሀገራችን የቆዳ ስፋት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ክፍል የአርብቶ አደር ማህበረሰቦች የሚኖሩበት አካባቢ እንደሆነ ይገመታል፡፡ በአብዛኛው በጠረፋማና ቆላማ የሀገራችን ክፍሎች የሚኖሩት አርብቶ አደሮች እጅግ አስከፊ በሆኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ተግዳሮቶች ውስጥ በቂ የመንግስት ትኩረት ሳያገኙ ረዥም ዘመን አልፏል፡፡ ቢያንስ ለአለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በሀገሪቱ የተፈራረቁ ስርአቶች የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ እና የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ልማት ትኩረት በመንሳት ህዝቡ በድህነት አዙሪት ውስጥ እንዲማቅቅ አድርገዋል፡፡ ከአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ህይወትና እና ደህንነት ይልቅ ለእንስሳቱ፣ ለሰፋፊና ለም የእርሻ መሬቱ እንዲሁም ሌሎች የከርሰ ምድር ሀብቶቹ ቅድሚያ ሲሰጡ የቆዩት የሀገራችን መሪዎች ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች በከፋ ሁኔታ የአርብቶ አደሩን ህብረተሰብ በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር ከፍተኛ በደል ፈጽመውበታል፡፡

የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ካሉበት ዘርፈ ብዙ የህይወት ውጣውረዶች የሚታደገው ልዩ የመንግስት ድጋፍ እና የፖሊሲ አማራጮች በእጅጉ የሚሻ ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ በሀገራችን ፖለቲካ በቂ ትኩረት አላገኘም፡፡ የአርብቶ አደሩን የህብረተሰብ ክፍል ካሉበት ተደራራቢ ችግሮች ለማላቀቅ፣ በሀገራችን ሁለንተናዊ ልማት ውስጥ በቂ ተሳትፎ እና ከልማቷም ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነእፓ የሚከተሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ይከተላል፡፡

 1. አርብቶ-አደሩ ማህበረሰብ ከተንቀሳቃሽ የኑሮ ዘይቤ ተላቆ ህይወቱን በተረጋጋ መንገድ መምራት የሚያስችለው የልማት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይሆናሉ፣
 2. አርብቶ-አደሩ ማህበረሰብ የተረጋጋ ኑሮ እንዲመሰርት የሚያስችሉት አነስተኛ መንደሮች ይገነባሉ፡፡ መንደሮቹ የተሟላ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ይኖራቸዋል፣
 3. የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችል የተቀናጁ የአርብቶ-አደር ልማት መርሀ-ግብሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ፤ የልማት መርሀ-ግብሮቹ በዋናነት ውሀን ማዕከል ያደረጉ ይሆናል፣
 4. አርብቶ-አደሩ ማህበረሰብ የአካባቢውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መምራት ይችል ዘንድ የተጠናከረና ሁሉን አቀፍ የአቅም ግንባታ ስራ ይሰራል፣
 5. የአርብቶ አደር ስልተ-ምርት በሀገሪቱ ህጎች በቂ እውቅና እንዲያገኝ፣ ለአርሶ አደርና ሌሎች ስልተ-ምርቶች የሚሰጠው ትኩረት እና የሚደረገው መንግስታዊ ድጋፍ ለአርብቶ አደሩም እንዲሰጥ የሚያደርጉ የህግ ማእቀፎች ይሰናዳሉ፣
 6. የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ኑሮ ከእንስሳቱ ህይወት እና ደህንነት ጋር እጅግ የተቆራኘ በመሆኑ ጥራት ያለው የእንስሳት እንክብካቤና የጤና አገልግሎት በመዘርጋት አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ብሎም አጠቃላይ ሀገራችንን ከእንስሳት ሀብታችን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ይዘረጋል፣
 7. የአርብቶ አደር አካባቢዎችን መልከዓ-ምድር፣ ስነ-ምህዳርና የአየር ፀባይ ወዘተ ታሳቢ ያደረጉ የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ለመንደፍ እና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ጥናቶች እና ምርምሮች ይደረጋሉ፤ በዘርፉ የተሳኩ ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችን ለመቅሰምና ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፣
 8. በአብዛኛው በቆላማ እና ጠረፋማ አካባቢ የሚኖረው አርብቶ-አደር ህዝባችን ከሌላው የሀገራችን ህዝብ ጋር ያለው የባህል እና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ተቀርጸው ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 9. የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አባላት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቃሽ ከመሆናቸው አንጻር ከሌሎች አርብቶ አደር ማህበረሰብ አባላት እና በአዋሳኝ ከሚገኙ አርሶ አደር ማህበረሰብ ጋር ለግጭት ስለሚዳረጉ ህይወታቸው ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ይህንን የአርብቶ አደሩን የደህንነት ስጋት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ፣
 10. የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግና ለማፋጠን ልዩ የበጀት ድጋፍ የሚደረግበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

የመሬት ይዞታና የባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ እና መሰረታዊ ጥያቄ ሆኖ ለረዥም ዘመናት የቆየ ቢሆንም የህዝብን ፍላጎት በተገቢው መንገድ ያገናዘበ፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ልማት በሚያፋጥን መልኩ መልስ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ የመሬት ይዞታና ባለቤትነት ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የስነ-ህዝብ፣ አካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከት ዘርፈ ብዙ የፖሊሲ አጀንዳ ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ መሬትን አስመልክቶ የሚቀረጹ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ከፍተኛ የንድፈ ሀሳብ እና ዓለም-ዓቀፍ የተግባር ተሞክሮን ያገናዘቡ ሊሆኑ እንደሚገባ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በፅኑ ያምናል፡፡ የመሬት ይዞታና ባለቤትነት ጥያቄ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግናና ልማት ያለውን ከፍተኛ ሚና ታሳቢ በማድረግና የመሬት ጥያቄ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ የነበረውን ከፍተኛ ቦታ ከግምት ውስጥ በማገባት ነእፓ መሬትን አስመልክቶ የሚከተሉትን ፕሮግራሞች ይከተላል፡፡

 1. በገጠርም ይሁን በከተማ የሚገኝ መሬት የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሲሆን መሬትን የማስተዳደር ኃላፊነት የመንግስት ይሆናል፣
 2. በገጠር ለእርሻ አገልግሎት የሚውል መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለአርሶ አደሮች ይሰጣል፣ ገበሬዎች በይዞታቸው ስር በሚገኝ መሬት ላይ ያሏቸው መብቶች እና ጥቅሞች ሳይሸራረፉ ይከበራሉ፣
 3. ገበሬዎች በግል ይዞታቸው ስር ያለን መሬት የማከራየት መብት ይኖራቸዋል፤
 4. ነእፓ የሀገራችንን ሁለንተናዊ የእድገት ደረጃ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ መሬትን በሂደት ሙሉ ለሙሉ መሸጥና መለወጥ የሚቻልበት የፖሊሲ አቅጣጫ ሊከተል ይችላል፤ ይህ አሰራር ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ እና ማህበራዊ እድገት ጋር ተገናዝቦ በጥናት የሚወሰን ይሆናል፣
 5. የከተማ መሬትን በተመለከተ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ለመገንባት ለሚጠቀሙበት መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ህጋዊ ሰነድ እንዲያገኙ ይደረጋል፣ በይዞታቸው ስር ባለ መሬት ላይ ያሏቸው መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ የህግ ዋስትና ይሰጣል፣
 6. የአርብቶ አደር አካባቢዎች ለአርብቶ አደሩ እንስሳት ግጦሽ የሚያገለግል መሬት በወል ይዞታ ሊቆይ ይችላል፣
 7. በገጠርም ሆነ በከተማ ለልማት ስራዎች ከመሬታቸው ለሚለሱ ዜጎች የክልል መስተዳድሮች ወይም የማዕከላዊ መንግስት ተገቢውን ካሳ በገንዘብ ወይም በአይነት ይከፍላሉ፣
 8. ሰፋፊ እና ዘመናዊ እርሻ እና የእንስሳት እርባታ ስራ ላይ ለመሰማራት ለሚሹ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች መንግስት መሬትን በሊዝ ያከራያል፣
 9. የሀገራችን የመሬት ፖሊሲና አስተዳደር ከሀገሪቱ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ በመሬት ይዞታ፣ ባለቤትነት እና አስተዳደር ዙሪያ ተከታታይ እና አሳታፊ ጥናቶች ይደረጋሉ፡፡

መሰረተ-ልማት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ልማት የጀርባ አጥንት ነው፡፡ በዓይነትና በብዛት ሰፊ የመሰረተ ልማት መኖር ምርትንና ምርታማነትን ለማሳለጥ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ንግድን ለማሳደግ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ የምርት ዋጋን ለማረጋጋት፣ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ወዘተ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ መሰረት ልማት መንገድ፣ የኃይል አቅርቦት፣ ግድቦች፣ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ትራንስፖርት፣ ቴሌኮሚኒኬሽን፣ የተፈጥሮ ጋዝ ወዘተ የሚያካትት ሲሆን ዘርፉን ለማሳደግና ለልማት ያለውን አስተዋፅዖ ከፍ ለማድረግ የሚከተሉት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

 1. የትራንስፖርት አገልግሎትን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ የመንገድ፣ የባቡርና እና የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት አውታሮች በስፋት ይገነባሉ፣
 2. በፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ ካለው የሀገራችን ህዝብ ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታ ይዘረጋል፣ በተለይም በከተሞች አካባቢ ያለውን ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ዘመናዊ እና አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲገነቡ ይደረጋል፣
 3. የግሉ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ ማበረታቻና ድጋፍ ይሰጣል፣
 4. በሀገር አቀፍ ደረጃ የመሰረተ ልማት አውታር ስርጭት ፍትሀዊ እንዲሆን ልዩ ትኩረት ይደረጋል፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አዋጭነት ባላቸው የጠረፍ እና ዝቅተኛ (Low land) አካባቢዎች የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማስፋ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፣
 5. ሀገራችን ያለባትን የሀይል አቅርቦት እጥረት ለመቀነስና በቂ እና አስተማማኝ የሀይል አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት እንዲጨምር ይደረጋል፣
 6. ከጎረቤት ሀገሮች እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ያለውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስሮችን ለማጠናከር ሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት፣ የኃይል፣ የቴሌኮም ወዘተ አውታሮች ከጎረቤት ሀገሮችና ከሌሎች ዓለም-ዓቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይገነባሉ፣
 7. ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በመስማማትና በቅንጅት በመስራት ፈጣንና አስተማማኝ የወደብ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚቻልበት አሰራር ይዘረጋል፤ ከሀገራቱ ጋር በመደራደርም ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ወደብ እንዲኖራት ለማድረግ ነእፓ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።
 8. ፈጣንና ጥራት ያለው የኢንተርኔትና ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ይደረጋል፣ የኢንተርኔት አገልግሎት በመላው የሀገሪቱ ክፍል በጥራት እንዲዳረስ ይሆናል፣
 9. የሎጂስቲክ ስርዓቱ እንዲዘምንና በዓለም-አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ተቀርጸው ተግባራዊ ደረጋሉ፣
 10. የሀይል አቅርቦት እጥረትን ለመቀነስና ተደራሽነቱን ለመጨመር አማራጭ የኃይል ምንጮች (off gride) ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፣ ታዳሽ ሀይል ትኩረት እንዲሰጣቸው ይደረጋል፣
 11. ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተማጣጣኝ የሀይል አቅርቦት ይኖር ዘንድ በሀገር ውስጥ የነዳጅ ፍለጋና የማልማት ስራ ይሰራል፣ የነዳጅ ክምችት ይኖርባቸዋል ተብለው በሚገመቱ አካባቢዎች የተጠናከረ የፍለጋ ስራ ይሰራል፣
 12. በከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የተገነቡ የመሰረተ ልማት አውታሮች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት በጥራት ይሰጡ ዘንድ ተገቢ ጥገናና እንክብካቤ እንዲያገኙ ይደረጋል፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ የመሰረተ ልማት አስተዳደር ስርአት ይዘረጋል፡፡

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ንግድ ለአንድ ሀገር ልማት ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቀልጣፋ፣ ቀላል እና የተቀናጀ የንግድና ኢንቨስትመንት ስርዓት ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገትና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የግብርና እና አምራች ኢንዱስትሪን በማሳለጥና በማቀናጀት ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን ለማሳካት የሀገር ውስጥና የውጭ ንግድን ማዘመንና ጠንካራ የፖሊሲ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፈጣንና ዘላቂ ልማት፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊስካል ፖሊሲ፣ በቂ የካፒታል ፍሰት፣ ሁነኛ የሀብት አጠቃቀም፣ ቀልጣፋ የንግድና የኢንቨስትመንት አካባቢ ይፈልጋሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሚከተሉትን የንግድና የኢንቨስትመንት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል፡፡

 1. የንግድና የኢንቨስትመንት ህጎች ከሌሎች የልማት ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ጋር እንዲቀናጁና እና እንዲተሳሰሩ ይደረጋል፣
 2. የሀገራችን የንግድ ህጎች ከአዓለም-ዓቀፍ የንግድ ስርዓት እና የአሰራር ደንቦች ጋር በሚጣጣም፣ ዓለም-ዓቀፍ ተወዳዳሪነትን በሚያረጋግጥ እና ሃገራችንን የተሻለ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ይሻሻላሉ፣
 3. ሀገራችን ውስጥ በተለያዩ የስራ መስኮች ለመሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች በአጭር ጊዜ እና በተቀላጠፈ መንገድ የኢንቨስትመንት ስራቸውን መጀመር እና ማካሄድ የሚያስችል አሰራር ይዘረጋል፣
 4. ከጎረቤት ሀገሮችና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ያለንን የሸቀጥና የአገልግሎት ንግድ ትስስር ከፍ ለማድረግ ስርነቀል የፖሊሲ ማሻሻያ ስራ ይሰራል፣
 5. በአብዛኛው የግብርና ምርቶችን በመላክ ላይ የተመሰረተው የሀገራችን የውጭ ንግድ ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲያካትት በማድረግ (Product Diversification) በግብርናና ጥሬ እቃዎች ዋጋ መዋዠቅ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ቀውስ እንዲቀንስ ይደረጋል፣
 6. ከውጭ የምናስመጣቸውን ምርቶች በመቀነስና ወደ ውጭ የምንልካቸውን በመጨመር የሀገራችን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቀነስ ብሎም የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬና የንግድ ሚዛን እንዲኖር የሚያደርጉ አሰራሮችና ፖሊሲዎች ተቀርጸው ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 7. የተመጣጠነ የውጭ ንግድ ስርዓት ለመፍጠር የሚረዱ የንግድና የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 8. የሀገራችን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የቀረጥና የካፒታል ፍሰት ስርአት ይዘረጋል፣
 9. ሀገራችን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ትሆን ዘንድ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ ከድርጅቱና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ድርድር ይካሄዳል፣
 10. ኢትጵያውያን ባለሀብቶችና የውጭ ኢንቨስተሮች በንግድና ኢንቨስትመንት ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅት ላይ በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፉ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፣
 11. የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) ለመሳብ የሚያስችል ምቹ የንግድና የኢንቨስትመንት ስርዓት ይዘረጋል፣
 12. ውጤታማ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ የሀገራችን ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሚሰሩበት አሰራር እንዲጠናከር አስፈላጊው የህግ እና የፖሊሲ ድጋፍ ይደረጋል፡፡

ቱሪዝም በብዙ ሀገራት ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየሰፋ የመጣ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው:: ቱሪዝም ለአንድ ሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማመንጨት በተጨማሪ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ ድህነትን በመቀነስና ዘላቂ ልማትን በማፋጠን ረገድ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶች ያሏት ሀገር ናት። ሆኖም ሀገራችን ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም ሀብት በተለያዩ ማነቆዎች ምክንያት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ሳታገኝ ቆይታለች። ቱሪዝም ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና በዘርፉ ውስጥ የሚታዩ ማነቆዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነእፓ ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሚከተሉትን ፕሮግራሞች ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል።

 1. ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሏትን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና ባህላዊ የቱሪስት መስህቦች መጠበቅና መንከባከብ፤
 2. አሁን ካሉት ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና ባህላዊ መዳረሻዎች በተጨማሪ የመዝናኛ ቱሪዝም፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ የትምህርት ቱሪዝም፣ የህክምና እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን የማበልፀግ ስራ ይሰራል፣
 3. ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችንና የመዝናኛ ተቋማትን፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማካሄድ የሚያስችሉ ሁለገብ አዳራሾችን፣ የህክምና አገልግሎት ተቋማትን፣ የመጓጓዣና የመገናኛ አውታሮችንና ሌሎች የመሰረተ ልማቶችን አቅርቦት ለማስፋት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ፣
 4. አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ በማስፈንና የቱሪስቶችን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ለቱሪስቶች ምቹ ከባቢ እንዲፈጠር የተቀናጀ ስራ ይሰራል፣
 5. ሀገራችን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያላትን አሉታዊ ስም (ድርቅ፣ ረሀብ፣ ግጭት፣ ወዘተ)በመቀየር በምትኩ የሀገራችንን አዎንታዊ ገፅታ የሚያሳዩ፣ ብርቅና ድንቅ የቱሪስት መዳረሻዎችን አጉልተው ማሳየት የሚችሉና ዓለም ዓቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ይሰራሉ፣
 6. በቱሪዝም መስክ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያድግ የተለያዩ ማበረታቻዎችና ድጋፎችን ይሰጣሉ፣
 7. በዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ እጥረት በመቅረፍ ጠንካራ የቱሪዝም ስርዓት ይዘረጋል፣
 8. በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ከዘርፉ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስርዓት በመፍጠር ዜጎች ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት በንቃት እንዲሳተፉ እና ባለድርሻ እንዲሆኑ ይደረጋል፣

የሀገራችን አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ እና የውጭ ምንዛሬን ከመፍጠር አንጻር ያለው ሚና ዝቅተኛ ሲሆን ይህም ዘርፉ ለጠቅላላው ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጾ እጅግ አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ዘርፉ ኋላ ቀር ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ሲሆን ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ የሀገራችን የኢንዱስትሪ ምርቶች በዓይነትም በብዛትም ትንሽ ናቸው፡፡ ነእፓ በሀገራችን የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት የሚከተሉትን ፕሮግራሞች ይከውናል፡፡

 1. ዘርፉን አሁን ካለበት ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የግል ባለሀብቶች በከፍተኛ ደረጃ ተሳታፊ የሚሆንበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ይሰጣል፣
 2. የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንዲስፋፉ ይደረጋል፣
 3. ለማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት የሚያግዙ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉና በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ለዘርፉ እድገት ድጋፍ የሚያደርጉበት አሰራር ይዘረጋል፣
 4. አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ የትራንስፖርትና ኮሙኒኬሽን አውታሮች ወዘተ ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ይደረጋል፣
 5. የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ከተለያዩ ተቋማት ለሚመረቁ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ የተቀናጀ ስራ ይሰራል፣
 6. የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ከግብርናው ዘርፍ ጋር በገበያና በግብዓት አቅርቦት ተመጋጋቢና ተደጋጋፊ እንዲሆኑ በማድረግ የሀገር ውስጥ ምርት በጥራትና በበቂ ሁኔታ እንዲመረት ማድረግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን መቆጠብና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ የሚቻልበት ፖሊሲ እና አሰራር ይዘረጋል፣
 7. የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማምረት የሚያስፈልጉ የማምረቻ ማሽነሪዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግና በቀላሉ በሀገር ውስጥ የማይመረቱትን በአጭር ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡበት ሁኔታ ይመቻቻል፣
 8. በሀገሪቱ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ማዕከላት የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈልገውን የሰው ኃይል በማሰልጠንና የቴክኖሎጂ አማራጮችን በማቅረብ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል፣
 9. በስራ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በመለየትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ምርታማነታቸው እንዲያድግ የሚያስችል አሰራር ይቀየሳል፣
 10. ሀገር በቀል የዕደ-ጥበብ ስራዎች እንዲስፋፉና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው አስተዋፅዖ ከፍ እንዲል ልዩ ድጋፍ ይደረጋል፣
 11. ቀጣይነት ያለው የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት እውን እንዲሆን ለማድረግ ኢንዱስትሪዎች በማህበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ቀድሞ መለየት የሚያስችል ዘመናዊ የኢንዱስትሪ አስተዳደርና ቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ኢንዱስትሪዎች በአካባቢና በዜጎች ማህበራዊ ህይወት ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አሉታዊ ተጽዕኖ የሚቀንስ አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል፣
 12. የኢንዱስትሪ ሴክተሩን የሚያበረታታ በጥናት ላይ የተመሰረተ የታክስና የቀረጥ ፖሊሲ ተግባራዊ ደረጋል፣
 13. በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፣ የክልሎቹን የተፈጥሮ ሀብት አቅምና ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መንደሮች እንዲስፋፉ ይደረጋል፡፡

2.9.1 የገንዘብ እና ፊስካል ፖሊሲ

የገንዘብ ፖሊሲ (Monitary Policy) የአንድን ሀገር አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመምራትና ለመቆጣጠር ብሎም በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖር የገንዘብ መጠንና ፍሰትን ለመወሰን የሚያገለግል የፖሊሲ መሳሪያ ነው፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ መሰረታዊ ዓላማ የሀገር ውስጥ አጠቃላይ የምርት እድገትን፣ የዋጋ ግሽበትን፣ የስራ እድል ፈጠራን፣ እና የውጭ ምንዛሬን ሁነኛና የተሻለ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በየጊዜው የሚዋዥቀውን የሀገራችን ማክሮ-ኢኮኖሚ ለማረጋጋት በመረጃ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ መቅረጽ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ዓላማዎች እውን ለማድረግ ይሰራል፡፡

 1. የገንዘብ ፍሰትን በመቆጣጠር የሀገራችን ገንዘብ (ብር) የመግዛት አቅሙ የተረጋጋ እንዲሆን ሳይንሳዊ እና በጥናት የተደገፉ ርምጃዎች ይወሰዳሉ፣
 2. በገበያ የሚመራና አስፈላጊም ሲሆን የመንግስት ቁጥጥር የሚደረግበት የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት በመዘርጋት የውጭ ምንዛሬ የተረጋጋ እንዲሆን ይደረጋል፣
 3. የካፒታል ፍሰትን ከሀገር ኢኮኖሚ ልማት ጋር የተጣጣመ በማድረግ የተረጋጋ የዋጋ መጠን እና የውጭ ምንዛሬ እንዲፈጠር ይደረጋል፣
 4. የሀገር ውስጥ የቁጠባ አቅምን በማሳደግ ለልማት የሚውል በቂ የካፒታል አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ፣
 5. የኢኮኖሚ መቀዛቀዝንና ድብርትን (Recession and depression) ለመከላከል የሚረዱ የገንዘብ ፖሊሲ ርምጃዎች ይወሰዳሉ፣
 6. የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን ሁለንተናዊ አቅም በማጠናከር በሀገሪቱ ጤናማ የገንዘብ ፖሊሲ እና የገንዘብ አስተዳደር ስርአት እንዲኖር ይደረጋል፡፡

2.9.2 የመንግስት በጀት እና እዳ

የአንድን ሀገር የማክሮ-ኢኮኖሚ እድገት እና ይዘት ከሚወስኑት ነገሮች መካከል የመንግስት በጀትና ብድር ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡ የተመጣጠነ የመንግስት ገቢ እና ወጪ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖር ከፍተኛ ሚና ይጫዋታል፡፡ ከፍተኛ የዋጋ ንረትን ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል ገቢን ያላገናዘበ ከፍተኛ የመንግስት ወጪና ብድር ናቸው፡፡ ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መንግስት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ባንኮች፣ ከዓለም ዓቀፍ አበዳሪ ድርጅቶችና ከሌሎች አካላት የሚበደረው ገንዘብ ኢኮኖሚው እንዳይረጋጋ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፡፡ በእዳ የሚገኝ ገንዘብ የረዥም ጊዜ ጥቅም በሌላቸው እና በሚገባ ባልተጠኑ ፕሮጀክቶች ላይ ሲውል ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳቱ ድርብርብ ይሆናል፡፡ ያልተመጣጠነ የመንግስት በጀትና እዳ ለሀገራችን ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ከፍተኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከመንግስት በጀት እና እዳ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ለመፍጠር የሚከተሉት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

 1. የመንግስት ጠቅላላ ወጪ ከገቢ ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን የሚያስገድድ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የመንግስት ወጪ ከተለያዩ ምንጮች ከሚሰበስበው የመንግስት ገቢ ጋር እኩል ወይም ተቀራራቢ እንዲሆን ይደረጋል፣
 2. የመንግስት የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ያለው ምጣኔ ወይም መጠነ-ጉድለት (Budget deficit/GDP ratio) ለጤናማ ኢኮኖሚ ከሚያስፈልገው ደረጃ እንዳያልፍ የቁጥጥር ስርአት ይዘረጋል፣
 3. የሀገሪቱ የብድር ጫና ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ያለው ምጣኔ ወይም መጠነ-ብድር (Debt/GDP ratio) በህግ እንዲወሰን በማድረግ መንግስት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የመበደር ስልጣኑ እንዲገደብ የህግ ማዕቀፍ ይበጃል፣
 4. የመንግስት የበጀት ስርዓትን በማጠናከር ዘላቂ ልማታችንን የሚያውክ እና ለከፍተኛ የወለድ ክፍያ የሚዳርግ ብድርን ለመከላከል የሚያስችል አሰራር ይዘረጋል፣
 5. የመንግስትን ገቢ ለማሳደግ ተከታታይ፣ ሳይንሳዊና በጥናት ላይ የተመሰረተ የታክስ ማሻሻያ ፕሮግራም ይካሄዳል፣ የግብር ዓይነቶችና መጠን እንዲሻሻሉ ይደረጋል፣
 6. ሁለቱን የማክሮ-ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን፣ ማለትም የዋጋ ግሽበትና ስራ አጥነት፣ በማመጣጠን የተረጋጋ የማክሮኢኮኖሚ አውድ ለመፍጠር የሚረዱ የተቀናጀ የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲ ስርአቶች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

2.9.3 የፋይናንስ ተቋማት

ፋይናንስና የፋይናንስ ተቋማት የሀገራችንን ኢኮኖሚ በማሳደግ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና እና ድርሻ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የፋይናንስ ስርዓትና ተቋማት እንዲገነቡ ጥረት ይደረጋል፡፡ ቀልጣፋና ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓት ለንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ ለስራ ዕድል መፈጠር፣ ለተረጋጋ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት፣ ለድህነት ቅነሳ፣ ለዘላቂ ልማት ወዘተ የማይተካ ሚና አለው፡፡ የሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት ብዛትና አሰራር ዝቅተኛ ሲሆን ለብሄራዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ያለው አስተዋፅዖም ዝቅተኛ ነው፡፡ ዘርፉ ያለበትን ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍና ለልማት ያለውን አስተዋፅዖ ከፍ ለማድረግ የሚከተሉት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

 1. የፋይናንስ ተቋማት የብድር አሰጣጥ ስርዓት ዘላቂ ልማትን፣ የተመጣጠነ ክልላዊ ዕድገትን፣ የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያግዝ ይሆን ዘንድ የተሻሻሉ የባንክ ስራ አዋጅ እና መመሪያዎች ይዘጋጃሉ፣
 2. የፋይናንስ ተቋማት የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በሚያግዙ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያበረታታ አሰራር ይቀየሳል፣
 3. ከወለድ ነጻ እና አካታች የባንክና የፋይናንስ ስርአት ተግባራዊ ይደረጋል፣
 4. ዘመናዊ የፋይናንስ ተቋማትን በብቃት የሚመሩና የሚያስተዳድሩ የፋይናንስ ባለሙያዎችን ማፍራት የሚችሉ የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲስፋፉ ድጋፍ ይደረጋል፣
 5. የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ጉልህ አስተዋጾ ማድረግ የሚችሉበት አግባብ እንዲፈጠር ቀልጣፋ እና አዋጭ አሰራሮች ይቀየሳሉ፣
 6. የገጠር የፋይናንስ ተቋማት እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ ድጋፍና ማበረታቻ ይደረጋል፣
 7. የሞባይልና የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ እና ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓቶችን በማስፋፋት የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ይደረጋል፣
 8. የፋይናንስ ተቋማትና አገልግሎት ስርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃ ፍትሀዊ እንዲሆን ይደረጋል፣ የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነት ከፍ እንዲል የሚያደርጉ የህግና አስተዳደራዊ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ፡፡