የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስታራቴጂ ዋነኛ ግብ በሀገር ውስጥ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እቅዶችን ለማሳካት የሚደረውገን ጥረት ማገዝ ነው፡፡ ነእፓ አገራችን ያለችበትን ጂኦ-ፖለቲካዊና ጂኦ ስትራቴጂያዊ እውነታዎች ታሳቢ በማድረግና በአፍሪካ ቀንድ፣ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ተለዋዋጭ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ሁነቶችን ከግንዛቤ በማስገባት ሀገራዊ ጥቅማችንን በተሻለ ሁኔታ ለማስከበር የሚያስችል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
ሀገራችን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ያላትን የረዥም ጊዜ ግንኙነት ታሳቢ ያደረገ፣ የሀገራችንንና የጎረቤት ሀገሮችን የጋራ ጥቅም በሚያስከብር የውጭ ግንኙነት መርህ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል፡፡ በአካባቢው የተንሰራፋውን ድህነትና ኋላቀርነት ለመታደግ እንደ ሀገር ከምናደርገው ከፍተኛ ርብርብ ጎን ለጎን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር አብሮ መስራት ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ የሚረዳው ፓርቲያችን ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ችግሮች፣ ስጋቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ የነእፓ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚከተሉትን ዋና ዋና ፕሮግራሞች ይይዛል፡፡
ከጎረቤት ሀገሮቻችን ጋር የረዥም ጊዜና የጠበቀ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለን፡፡ ከአንዳንዶቹ የጎረቤት ሀገራት ጋር በተለያዩ ጊዜና ምክንያቶች ቅራኔዎችና ግጭቶች የተከሰቱ ቢሆንም፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር እና ይበልጥ ማበልጸግ ይቻላል ብልን እናምናለን፡፡ የሀገራችንን የአጭርና የረዥም ጊዜ ጥቅሞችና ፍላጎት ለማሳካት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በመሆኑም ከሁሉም የጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመተማመን፣ በመከባበርና በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት መርህ ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡
ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሁለትዮሽ (Bilateral) እና የብዙዮሽ (Multilateral) ስምምነቶችንና የትብብር መድረኮችን በመፍጠር መልካም እድሎችን በጋራ ለመጠቀምና ስጋቶችን ለመከላከል በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መስራት ያስፈልጋል፡፡ ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሀገሮች ጋር ስትወዳደር በኢኮኖሚ፣ በቆዳ ስፋትና በህዝብ ብዛት ታላቅ ሀገር ነች፡፡ ያለንን የተሻለ አቅም ተጠቅመን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በጋራ በመስራት የህዝባችንንና የጎረቤት ሀገራት ህዝቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን እንቀይሳለን፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ)፣ ከምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ እና ከሌሎች መሰል ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ የፖሊሲ ማዕቀፎች ተቀርጸው ተግባራዊ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
ዓለም ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታና ሀገራችን ካለችበት ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ በመነሳት በተለይ በኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ ወታደራዊ፣ የቴክኖሎጂና ፖለቲካዊ አቅማቸው ከፍተኛ ከሆኑ ኃያላን ሀገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በተቻለ መጠን ከሁሉም ሀገራት ጋር ሚዛናዊና የሀገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ ግንኙነታችን እንዲጠናከር ይደረጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ከአሜሪካን፤ አውሮፓ ህብረት፤ ቻይና፣ መካከለኛውና ሩቅ ምስራቅ ሀገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት ከየሀገራቱ ጋር የነበረንን ታሪካዊ ግንኙነት፣ ያለንን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የባህል ትብብር ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተቀይሶ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም-ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚኖረን ግንኙነት የሀገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ይበልጥ በሚያስከብር እና ሀገራችን ለዓለም ሀገራትና ህዝቦች ሰላምና ልማት የድርሻዋን እንድታበረክት በሚያስችል መንገድ ተነድፎ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡