ላለፉት ጥቂት ቀናት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት እና በህወኃት መካከል በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የነበረው የሰላም ድርድር በዛሬው እለት በስምምነት መጠናቀቁ ታውቋል፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሁለት አመት ያስቆጠረውን እጅግ አውዳሜ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ለተደረሰው ስምምነት ያለውን ከፍተኛ ድጋፍ እየገለጸ ለድርድሩ መሳካት በጎ አስተዋጾ ላደረጉ አካላት ሁሉ አድናቆቱን ይገልጻል፡፡
ልክ የዛሬ ሁለት አመት ጥቅምት 24፣ 2013 የተለኮሰው የጦርነት እሳት ባለፉት 24 ወራት ሀገራችንን እና ህዝባችንን ከፍተኛ የህይወት፣ የንብረት እና የስነልቦና ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ ይፈታ ዘንድ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በዛሬው እለት ለተደረገው ስምምነት ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣል፡፡
በዛሬው እለት ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች ወደ ተግባር ተለውጠው መላው የሀገራችን ህዝቦች በጉጉት የሚጠብቁት ሰላም እና መረጋጋት እውን ይሆን ዘንድ ዋነኛ ተደራዳሪዎቹ የፌዴራል መንግስት እና ሕወኃት፣ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲሁም መላው የሀገራችን ህዝቦች ለስምምነቱ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ይወጡ ዘንድ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ጥሪ እያቀረበ፣ በዛሬው እለት በተደረሰው የሰላም ስምምነት ለመላው የሀገራችን ህዝቦች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
መጪው ዘመን በሀገራችን ሰላም፣ ወንድማማችነት፣ አንድነት፣ ልማት እውን ይሆን ዘንድ አጥብቀን እንመኛለን፡፡
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ጥቅምት 23፣ 2015
አዲስ አበባ
