ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted by contenteditor@… on Thu, 11/05/2020 - 12:26

በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል!!

ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ተገድለዋል፣ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ ሀብት ንብረታቸው ወድሟል እንዲሁም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች በዋናነት ማንነትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸው ወንጀሉን ይበልጥ ውስብስብ እና አደገኛ አድርጎታል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በዜጎች ላይ የሚደርስ የትኛውም አይነት ጥቃት በተለይም ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የሀገራችንን ሰላም እና አንድነት፣ የዜጎችን አብሮነት ክፉኛ የሚፈታተኑ በመሆናቸው በአፋጣኝ ሊቆሙ ይገባል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን፣ በደቡብ ክልል በጉራ ፈርዳ ወረዳ እና በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንጹሀን ዜጎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች በሀገራችን ያለውን እጅግ አሳሳቢና በቀላሉ ተሰባሪ የደህንነት ሁኔታ በግልጽ ያመላክታል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በዜጎች ህይወት እና ደህንነት ላይ የሚደርስን ማናቸውም ዓይነት ጥቃት በእጅጉ ያወግዛል። ጠባብ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደረግ ጥቃት እጅግ የሚወገዝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ ሁሉም ሰላም ወዳድ ኃይሎች በአንድነት ሊያወግዙት ይገባል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣውን በንጹሀን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን አሳዛኝ ጥቃት ለማስቆም፣ በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን፣ ለግጭት እና ለዜጎች ሞት የሚዳርጉ ጥላቻ እና ቁርሾዎችን ለመቅረፍ አፋጣኝ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ መደረግ አለበት ብሎ ያምናል።

በንጹሀን ዜጎች ህይወት ላይ አደጋ በሚፈጽሙ ኃይላት ላይ የፌደራል እና የክልል መንግስታት በቂ እና አስተማማኝ እርምጃ አለመውሰዳቸው፣ በየጊዜው የሚደርሱ ጥቃቶች ምንነት እና መንስኤ እንዲሁም የድርጊቱን ፈጻሚዎች በፍጥነት በመለየት ለህዝብና ለፍትህ አለማቅረባቸው ጸረ-ሰላም ኃይላት በዜጎች ላይ የሚያደርስቱን ኢ-ሰብአዊ ጥቃት እንዲቀጥሉበት እድል ሰጥቷቸዋል።

በዜጎች ላይ የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን “ያልታወቁ ቡድኖች በዜጎች ላይ ጥቃት ፈጸሙ” የሚሉ መግለጫዎች እየሰጡ ማለፍ ለዜጎቸ ህይወት እና ደህንነት ደንታ ቢስነት ከመሆን በተጨማሪ ወንጀለኞችን የሚያበረታታ ተግባር ነው። በመሆኑም መንግስት ህግ እና ስርአትን በሚተላለፉ ኃይሎች ላይ ፈጣን እና ተገቢ እርምጃ በመውሰድ ከምንም በላይ የዜጎችን ህይወት፣ ንብረት፣ ሰላም እና ደህንነት ሊጠብቅ ይገባል። መንግስት ኃይል የመጠቀም ብቸኛ መብቱን በመጠቀም በጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ህይወት እና ደህንነት የመጠበቅ የህግ፣ የሞራል እና የታሪክ ተጠያቂነት አለበት።

ነእፓ ብሄራዊ ውይይት እና መግባባት እንዲፈጠር በተደጋጋሚ ሀሳብ ሲያቅርብ የቆይ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ሞት እና ስቃይ ለማስቆም ዛሬም አፋጣኝ ብሄራዊ ውይይት እና መግባባት እንዲፈጠር ጥሪውን በድጋሜ ያቀርባል። በተለይ መንግስት እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገራችን ላይ ያንዣበበውን የግጭትና የጦርነት አደጋ ከስር መሰረቱ ለመቅረፍ ተቀራርበው ሊሰሩ እና ዘላቂ መፍትሄ ሊያበጁ የሚገባባት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን።

በዜጎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር እና እንዲባባስ የሚያደርጉ ምክንያቶችን ለማስቆም በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶች እና የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ነእፓ ያስገነዝባል።

መላው የሀገራችን ህዝቦች፣ መንግስት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ኢ-ሰብአዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፡፡

ጥቅምት 23 2013

አዲሰ አበባ፡፡