ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted bycontenteditor@… onTue, 06/01/2021 - 09:33

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በጋምቤላ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ፡፡

አዲስ አበባ::

*********************************************************************

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ከጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን) እና የጋምቤላ ህዝብ ፍትህ፣ ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህፍሰልዴን) ጋር በ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ አብሮ ለመስራት የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓት ወቅት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር ዶክተር አብዱልቃድር አደም እንደተናገሩት ስምምነቱ ህብረ-ብሔራዊነትን ያጠናክራል፤ በጋራ አብሮ የመስራት ባህልን ያዳብራል፤ በውጤቱም ህዝብ አሸናፊ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን) እና የጋምቤላ ህዝብ ፍትህ፣ ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህፍሰልዴን) መሪዎች በበኩላቸው የትብብር ስምምነቱ በምርጫው ዙሪያ ብቻ እንደማይወሰንና ከምርጫው በኋላም አብሮ ለመስራት የሚያስችል ማዕቀፍ ኖሮት ትብብሩ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚደርስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ድምጻቸውን ለሁለቱ ፓርቲዎች ማለትም ለጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና ለየጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ለሰላምና ልማት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይሰጣሉ፡፡ ከጋምቤላ ክልል ውጪ የሚገኙ የሁለቱ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች በበኩላቸው ድምጻቸውን ለነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ይሰጣሉ፤ ፓርቲዎቹም የምርጫ ቅስቀሳ ስራዎችን በጋራ ያከናውናሉ፡፡

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ከዚህ ቀደም በሶማሌ ክልል ከሚገኙ ፓርቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት መፈራረሙን ያስታወሱት ዶክተር አብዱልቃድር በቀጣይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ለማድረግ ፓርቲው በሂደት ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹እኩልነት በተግባር!››

‹‹ህብረ-ብሔራዊነት በተግባር!››

news image
News Category