ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ እና የአፋር ህዝብ ፓርቲ በምርጫ ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማሙ፡፡
አዲስ አበባ
***********************************************************************
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) እና የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችላቸውን ስምምነት በትላንትናው እለት በግዮን ሆቴል ተፈራርመዋል፡፡
የስምምነቱ ዋና ዓላማ ሁለቱ ፓርቲዎች በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል አሰራር መፈጠር ነው፡፡
ስምምነቱ ቀደም ሲል በነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) እና በአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) መካከል በክልላዊ እና ሀገራዊ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች ውጤት እንደሆነ በስምምነት ሰነዱ ላይ ተመልክቷል፡፡
የስምምነት ሰነዱን የፈረሙት የነእፓ ሊቀ መንበር ዶ/ር አብዱልቃድ አደም እና የአፋር ህዝብ ፓርቲ ኃላፊ አቶ ሙሳ አደም ስምምነቱ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን ትብብር ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በፓርቲዎቹ መካከል በተደረሰ ስምምነት መሰረት ነእፓ በአፋር ክልል እጩዎችን ያላቀረበ ሲሆን፣ በአፋር ክልል የሚገኙ የነእፓ አባላት እና ደጋፊዎች የአፋር ህዝብ ፓርቲ እጩዎችን እንዲመርጡ፣ በተመሳሳይ ከአፋር ክልል ውጪ የሚገኙ የአፋር ህዝብ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች የነእፓን እጩዎች እንዲመርጡ ስምምነቱ ይጠይቃል፡፡
ስምምነቱ ምንም እንኳ 6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ድህረ ምርጫ ሁለቱ ፓርቲዎች ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋር ለመፈጠር ለሚታሰበው ጠንካራ ጥምረት መሰረት ለመጣል የታቀደ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ነእፓ በሀገራችን ጠንካራ የፖለቲካ ስርአት እና የፖለቲካ ተቋማት ለመፍጠር በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ጠንካራ ትብብር ያስፈልጋል የሚል ጽኑ እምነት ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በሶማሊ እና ጋምቤላ ክልሎች ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የትብብር መድረክ መፍጠሩ ይታወሳል፡፡
ግንቦት 3 2013
አዲስ አበባ
