ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted by contenteditor@… on Mon, 01/06/2020 - 09:37

ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ በስልጤ ዞን መዲና ወራቤ  ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ አካሄደ፡፡ 

ታህሳስ 27/2012፣ አዲስ አበባ


 በስልጤ ዞን የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ማስተባበሪያ ቢሮ አዘጋጅነት እሁድ በስልጤ ዞን የባህል አዳራሽ የተካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ በርካታ የዞኑ ነዋሪ ታድሞበታል፡፡ በስብሰባው የተገኙ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ስብሰባውን በሃገረሰብ መልዕክት ከፍተዋል፡፡
 በህዝባዊ ስብሰባው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም  የስልጤ ህዝብ ለመልካም ስነምግባር ትልቅ ዋጋ  የሚሰጥ እንዲሁም በባህሉና ሃይማኖቱ የሚኮራ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ስልጣናቸውን ተጠቅመው የህዝብን ጥቅም ላይ ጉዳት የሚያደርሱ፣ በፌደራልና በክልል የተሻለ ስልጣን ለማግኘት ሲሉ የህዝብን ድምፅ የሚያፍኑ ገዢዎችን በፅናት ሲታገል የቆየ ህዝብ ነው ያሉት ሊቀንበሩ አሁን ላይ ከነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ጎን ቆመው መብታቸውን ለማስከበር መጀመራቸው የዚሁ የትግል ፅናታቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ 
ሊቀመንበሩ የስልጤ ዞን ማህበረሰብ  እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን ከገባንበት የጭቆናና የድህነት አዙሪት ወጥተን የተሻለች ጠንካራ የጋራ ሃገር ለመስራት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር ቋንቋና ሃይማኖት ልዩነቶች ሳንታጠር እንደ አንድ የሃገር ልጅ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ልንሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡ 
በዞኑ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጀማል ቡሴር በበኩላቸው ለስልጤ ማህበረሰብ  ማንነት መከበርና  ለዞኑ ሁለንተናዊ ልማት ሁሉም የዞኑ ነዋሪ ከነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ጎን ተሰለፎ እንዲታገል አሳስበዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ለህዝባዊ ስብሰባው ወደ ወራቤ ከተማ የገቡት የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የፓርቲው ደጋፊ የዞኑ ተወላጆች በወራቤ ኮምፕሪሄንሲቭ ሆስፒታል ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸው የስራ እንቅስቃሴዎችን ቃኝተዋል፣ ህሙማንን ጠያቀዋል፡፡ 

 

news image
News Category