ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted by contenteditor@… on Thu, 11/05/2020 - 09:19

የአንበጣ መንጋ በገበሬዎች ላይ በማድረስ ላይ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ አስቸኳይ ሀገራዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል!!

አደጋው በሺዎች የሚቆጠሩ ድሀ ገበሬዎችን ተስፋ አጨልሟል፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል፡፡ በተለይ በሰሜን እና በሰሜን ምስራቅ የሀገራችን ክፍሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከፊል የአማራ፣ የትግራይ እና የአፋር ክልል ገበሬዎችን እና አርብቶ አደሮችን እርሻ በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃ ሲሆን፣ ሊሰበሰብ የደረሰ ሰብል ሙሉ ለሙሉ አውድሟል፡፡

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የአካባቢው ህብረተሰብ፣ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ግብርና አካላት ባህላዊ እና ዘመናዊ (የኬሚካል ርጭት) መንገዶችን በመጠቀም መንጋውን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ ቢያደርጉም ችግሩ ከአካባቢው ማህበረሰብ አቅም በላይ በመሆኑ መቋቋም አልተቻለም፡፡ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ማሳ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በአንበጣ መንጋ ከተጠቁ አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል የደቡብ እና ሰሜን ወሎ እንዲሁም የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞኖች ይገኙበታል፡፡

ምርታማነቱ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የእርሻ ስራ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የሀገራችን ገበሬ፣ በከፍተኛ ድካም ያፈራው ሰብል በአንበጣ መንጋ ሲወድም ለከፋ ርሀብ፣ ለስደት እና ለሞት ይዳረጋል፡፡ ችግሩ በገበሬው ላይ ብቻ ሳይወሰን በሀገር ደረጃ የምግብ ሰብሎች ዋጋ መናር እና አጠቃላይ የምግብ ዋስትና ቀውስ ያስከትላል፡፡ የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋልታ በሆነው የእርሻ ዘርፍ የሚደርስ ጉዳት ከፍተኛ እና ውስብስ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችም ያስከትላል፡፡

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ ጋር ተደምሮ የዜጎችን በተለይም በመንጋው በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎችን ተስፋ አጨልሟል፡፡

በመሆኑም እንደ ሀገር የገጠመንን ይህንን የአንበጣ ወረርሽን ለመከላከል ህብረተሰቡ፣ መንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ዜጎች በዘርፈ ብዙ የሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮ አደጋዎች ለከፋ ጉዳት በተዳረጉበት በዚህ ወቅት፣ በተለይም የፌዴራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶቹን ቅደም ተከተል ሊፈትሽ ይገባል፡፡ መንግስት እንደ ሀገር ያለንን ውስን ሀብት እና አቅም አንገብጋቢ ካልሆኑ ፕሮጀክቶች በማዞር በአንበጣ እና በጎርፍ ከፉኛ የተጎዱ የአርሶ አደር እና አርብቶ አደር አካባቢዎችን ለመታደግና መልሶ ለማቋቋም ሊጠቀምበት ይገባል፡፡

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

መስከረም 30 2013

አዲስ አበባ፡፡

news image
News Category