ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted by contenteditor@… on Wed, 06/24/2020 - 16:15

የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለማጠናከር እና ለማዘመን የሚሰራ ስራ የሚደገፍ ነው፡፡

********************************************************************

የሀገርን ዳር ድንበር እና የዜጎችን ሰላም የመጠበቅ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት የተጣለበት የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ሀገር እና ህዝብ የጣሉበትን ታላቅ ኃላፊነት በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት እና በላቀ የሙያ ስነምግባር ግዳጁን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ሰራዊታችን ከአባቶቻችን የወረስነውን አኩሪ የጀግንነት ታሪክ አስጠብቆ ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ከውጪ እና ከውስጥ የተቃጡባትን አደጋዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ሲመክት ቆይቷል፡፡

የመከላከያ ኃይላችን ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን በማጠንከር በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ፣ በስትራቴጀ፣ በወታደራዊ ስልት… ራሱን እያደሰ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በፍጥነት በሚያድረገው የመከላከያና የደህንነት ኢንዱስትሪ ውስጥ የሀገር መከላከያ ኃይላችን ብቃቱን ጠብቆ በማንኛውም ጊዜ ሉአላዊነታችንን የሚፈታተኑ አደጋዎችን ለመመከት ተከታታይ እና የተሟላ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ይህንን እውን ለማድረግ የሀገራችን ኢኮኖሚ በሚፈቅደው ልክ በቂ ሀብት መመደብ የግድ ይላል፡፡

ከዚህ አንጻር በትላንትናው እለት ውይይት የተደረገበት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው እና የሚደገፍ እርምጃ ነው፡፡ የሀገራችን የመከላከያ ኃይል የሀገራችንን፣ የአካባቢያችንን እና የዓለምን ተጨባጭ ከግምት ውስጥ ያስገባ ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ እና ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በውይይቱ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደገለጹት ዋና ዓላማው የሀገሪቱን ህገ መንግስት ማስከበር የሆነ፣ ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ርእዮተዓለም እና ወገንተኝነት የራቀ፣ የሀገራችንን ህዝቦች ብዝሀነት ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ እና ዘመናዊ የሀገር መከላከያ መገንባት ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት እና ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ሰነዱ ውይይት የተደረገበት ወቅት ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቷን ለማስከበር ህዝብ እና መንግስት ከፍተኛ ርብርብ በሚያደርጉበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሀገራችን በየጊዜው የሚያጋጥሟትን የደህንነት ስጋቶች በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት የሚችል የሀገር መከላከያ ኃይል ለመገንባት የሚደረገውን ማንኛውን እንቅስቃሴ ይደግፋል፣ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ለማበርከት ይሰራል፡፡

ሰኔ 15፣ 2012

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ

news image
News Category