ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted by FEP@admin_123_ on Wed, 10/30/2019 - 17:13

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በልዩ ልዩ ዘርፎች ከ20 በላይ የፖሊሲ ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑ እና የተቋሙ ጉብኝት ለተጀመረው የፖሊሲ ዝግጅት ስራ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ተመልክቷል፡፡

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም ከፓርቲው ሰራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፖሊሲ ተቋምን (The Horn Economic and Social Policy Institute- HESPI ) ጎበኙ፡፡ ተቋሙ እ.አ.አ. በ2006 የተመሰረተ ሲሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች እና ለሌሎች በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገሮች የፖሊሲና የማማከር ስራዎችን የሚሰራ የምርምር ተቋም መሆኑ ታውቋል፡፡ HESPI ክልላዊ በሆኑ የማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የፖሊሲ ሀሳቦችን በማዘጋጀት ለመንግስትና መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት፣ ለግል ዘርፉ፣ ክልላዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያቀርባል፡፡

የነእፓ ልኡክ ከ HESPI የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በጥናትና መረጃ ላይ የተመሰረቱ ፖሊሲዎችን መቅረጽ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ለዚህም HESPI’ን የመሰሉ የምርምር ተቋማት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያና የሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መሰረታዊ ችግር በንድፈ ሀሳብ ያልተረጋገጡ፣ ሀገራዊና አካባቢያዊ እውነታዎችን ከግምት ያላስገቡ እና በስታትስቲካዊ መረጃዎች ያልተደገፉ በጥቂት የፖለቲካ መሪዎች እና ቡድኖች ፍላጎት የሚቀረጹ እና የሚተገበሩ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡  

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርምር ተቋማት ጋር በቅርበትና በትብብር መስራት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የገለጹት የነእፓ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃደር ፓርቲያቸው ከHESPI ጋር በትብብር  ለመስራት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ገልጸዋል፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በልዩ ልዩ ዘርፎች ከ20 በላይ የፖሊሲ ሰነዶችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑን የገለጹት የፓርቲው ኃላፊዎች በፖሊሲ ሰነዶቹ ዝግጅት ዙሪያ ነእፓ ከ HESPI እና ሌሎች መሰል የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልግ  አመልክተዋል፡፡

የተቋሙ የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል ፋንታየ የነእፓ ኃላፊዎች HESPI ን ለመጎብኘት እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ላሳዩት ተነሳሽነት አመስግነው፣ ነእፓ ተቋሙን የገበኘ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ተቋማቸው ምንም እንኳ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት እና መንግስት ጋር ግንኙነት የሌለው ገለልተኛ የምርምር ማዕከል ቢሆንም የሚያዘጋጃቸውን የፖሊሲ ጥናቶች ለተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እና ፖሊሲ አውጪ ድርጅቶች በምክር መልክ የሚያቀርብ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ነእፓ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋሙን እንደ አንድ የእውቀት እና መረጃ ምንጭ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

አቶ ዳንኤል HESPI ባለፉት አስር አመታት በበርካታ የፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ ዓለም ዓቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ልዩ ልዩ ጥናቶችን አካሂዶ ውጤቱን ለህትመት ያበቃ መሆኑን ገልጸው፣ የድህነት ቅነሳ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ክልላዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስር፣ የኢጋድ ሀገሮች ትብብር፣ ዘላቂ ልማት፣ መሰረተ ልማት፣ ከብዙ በጥቂቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ተጨባጭ የትብብር መስኮችን ለመለየት ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ትብብሩን ህጋዊ እና ዘላቂ ለማድረግ በድርጅቶቹ መካከል የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ተዘጋጅቶ እንዲፈረም በመስማማት ጉብኝቱ ተጠናቋል፡፡  

የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት አዲስ አበባ ሲሆን በሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ልዩ ልዩ የጥናት ፕሮጀክቶችን ከአፍሪካ ህብረት፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ኢጋድ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

news image
News Category