ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted by contenteditor@… on Wed, 06/17/2020 - 15:21

ዴሞክራሲዊ አንድት መሰረቱ ነጻነት እና እኩልነት ነው”

ዶ/ር አብዱልቃድር አደም፡ የነእፓ ሊቀ መንበር

“እኩል ያልሆነ እኩልነትን ኢ.ህ.አ.ፓ አይቀበልም”

አቶ ሰለሞን ተሰማ የኢ.ህ.አ.ፓ ተቀዳሚ ም/ሊቀ መንበር

*****************************************************************

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢ.ህ.አ.ፓ) የስራ አስፈጻሚ አባላት ከነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አመራሮች ጋር በድርጅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ውይይት አደረጉ፡፡

*****************************************************************

የኢ.ህ.አ.ፓ ከፍተኛ አመራሮች በነእፓ ዋና ጽ/ቤት ተገኝተው ከፓርቲው ሊቀመንበር ከዶ/ር አብዱልቃድር አደም እና ሌሎች የፓርቲው ኃላፊዎች ጋር በሁለቱ ፓርቲዎች ፖሊሲ፣ ፕሮግራም፣ ርእዮተ ዓለም፣ አደረጃጀት እና በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የነእፓ ሊቀመንበር ኢ.ህ.አ.ፓ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ የማይረሳ የተጋድሎ ታሪክ የሰራ አንጋፊ ፓርቲ መሆኑን ጠቅሰው ለረዥም ጊዜ ከሀገር ውጪ ከቆየ በኃላ በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ መንቀሳቀስ መጀመሩ ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው፣ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች የትኛውም ርእዮተ ዓለም፣ ታሪክ ወይም ፕሮግራም ካለው ህጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ጋር አብሮ ይሰራል ብለዋል፡፡

የለዘብተኛ ሊበራሊዝም ርእዮተ ዓለም እና ትምህርት ተኮር ብሄራዊ የልማት ስትራቴጂ (ENDS) የተሰኘ የፖሊሲ ማእቀፍ ያለው ነእፓ በሀገራችን የሚዛናዊ ፖለቲካ ጽንሰ ሀሳብን ለማስተዋወቅ እና ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን የነእፓ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የኢ.ህ.አ.ፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ኢብራሂም አብዱሰላም እና አቶ ቴዎድሮስ ዘርፉ በበኩላቸው ፓርቲያቸው ምንም እንኳን የቀድሞ ታሪኩ እንዳለ ቢሆንም 21ኛውን ክፍለ ዘመን የዋጀ ፖሊሲ እና ፕሮግራም ቀርጾ በነባር የኢ.ህ.አ.ፓ ታጋዮች እና በወጣት ኃይል በአዲስ መልክ ተደራጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ድርጅት መሆኑን ገልጸው ለህዝቦች የብሄር፣ የመደብ እና የእምነት እኩልነት የሚታገል ድርጅት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፖሊሲ አንጻር ኢ.ህ.አ.ፓ ትላንትም ሆነ ዛሬ ለድሀው የህብረተሰብ ክፍል ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚቆም ድሀ ተኮር (Pro poor) አቅጣጫ የሚከተል መሆኑን የገለጹት ኃላፊዎች በሀገራችን ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲሆን ኢ.ህ.አ.ፓ በርትቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ሰለሞን ተሰማ በሀገራችን “እኩል ያልሆነ እኩልነት” ለረዥም ዘመን ሰፍኖ የቆየ መሆኑንና ይህም ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት እንቅፋት እንደነበረ ገልጸው፣ በዜጎች መካከል እውነተኛ እኩልነት እንዲሰፍን ኢ.ህ.አ.ፓ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ፓርቲዎቹ አመራሮች ኢ.ህ.አ.ፓ እና ነእፓ በቀጣይ የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚሰሩበትን አግባብ ወደፊት በሚደረጉ ውይይቶች ለመነጋገር በመስማማት የእለቱን ውይይታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

ሰኔ 10፣ 2012

አዲስ አበባ፡፡

news image
News Category