ዜና ነ.እ.ፓ

አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!አዳዲስ ዜናዎችን ይከታተሉ!

Submitted by contenteditor@… on Fri, 06/19/2020 - 11:37

ሀገራዊ መግባባት ወቅታዊ እና ወሳኝ ብሄራዊ አጀንዳ ነው”

ዶ/ር አብዱልቃድር አደም፡ የነእፓ ሊቀ መንበር

*********************************************************

የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ አመራሮች ነእፓን ጎበኙ፡፡

*********************************************************

ዛሬ ከቀትር በኃላ በኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ ሊቀመንበር በአቶ መሀመድ አሊ መሀመድ የሚመራ የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ቡድን የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ከፓርቲው ሊቀመንበር ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

የስብሰባው ዋና አጀንዳ በሀገራችን ሁሉን አቀፍ የብሄራዊ መግባባት (National Dialogue) መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታን ማመቻቸት ሲሆን ከብሄራዊ መግባባት ጋር በተያያዘ ሁለቱ ፓርቲዎች በተለያየ ጊዜ ባዘጋጇቸው መነሻ ሰነዶች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የተራማጅ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሀመድ አሊ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ምስራቅ ፓርቲው “የብሄራዊ ውይይት አስፈላጊነት እና የተግባር ፍኖተ ካርታ”

በሚል ርእስ ያዘጋጀውን ሰነድ ይዘት በአጭሩ ያብራሩ ሲሆን ፓርቲው ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዶ/ር አብዱልቃድር የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ የምስረታ ሂደቱን በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብሄራዊ መግባባትን ዋና አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀሱ እና በዚሁ ዙሪያ መነሻ ሰነድ ማዘጋጀቱ እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ነእፓ በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ ባለፉት ወራት እያደረጋቸው ያሉ ስራዎችን ለቡድኑ ያብራሩት ዶ/ር አብዱልቃድር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የሀገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ይደር የማይባል አጀንዳ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ምርጫው በኮቪድ 19 ምክንያት ከመራዘሙ በፊት፣ ብሄራዊ መግባባት ከምርጫ በፊት መካሄድ እንዳለበት በማመን በጉዳዩ ላይ መነሻ ጽሁፍ አዘጋጅቶ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ነእፓ በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ነእፓ በአጀንዳው ዙሪያ ከኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በብሄራዊ መግባባት (National Dialogue) አብረው ሊሰሩ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

ሰኔ 10፣ 2012

አዲስ አበባ፡፡

news image
News Category