የፖለቲካ ፕሮግራም

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ በበርካታ የዓለም ሀገራት ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ እንደመጣ ይታመናል፡፡ የሊበራል አስተሳሰብ በዋናነት ለዜጎች የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነጻነት ትኩረት የሚሰጥ፣ የመንግስትን መጠንና ጣልቃ ገብነት በመገደብ ዜጎች በግልም ሆነ በጋራ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ እድል የሚሰጥ ስርአት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የተንዛዛ የመንግስት አሰራርን፣ ቢሮክራሲያዊ ንቅዘትን፣ የመንግስትን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ለማስቆም፣ ሙስናን በማስወገድ ፈጣንና ቀልጣፋ አሰራር እውን ለማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በተሻለ ሁኔታ ለማስከበር ይረዳል ተብሎ ይገመታል፡፡ የሊበራል አስተሳሰብ ሰፊ ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን፣ እንደ ሀገራት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የባህልና የቴክኖሎጂ እድገት ደረጃ በተለያየ መንገድ የሚተገበርና አንድ ወጥ መለኪያ የሌለው መሆኑ፤ እንደ ሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሊስተካከል መቻሉ ተቀባይነቱን ሊጨምር እና አተገባበሩም ምቹ እንዲሆን አስችሏል፡፡

በዚህ መሰረት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ራእዩን በተሳካ ሁኔታ እውን ለማድረግና ዓላማዎቹን ለማሳካት የሊበራል አስተሳሰብን ከሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ጋር አዋዶ ነባራዊ እና ተጨባጭ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እውነታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘብተኛ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም ይከተላል፡፡ የለዘብተኛ ሊበራል ርዕዮተ ዓለም የሊበራል አስተሳሰቦችን ከሀገራችን ታሪክ፣ ባህል፣ የህዝቦቿ ስነ-ልቦናና ማህበራዊ ልማዶች ጋር በማዋደድ ሀገራዊ እሴቶችን ለመጠበቅ ምቹ የፖለቲካ ምህዳር እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡ የለዘብተኛ ሊበራል አስተሳሰብ ለማህበራዊ እሴቶችና ግብረገብነት እውቅና የሚሰጥ ሲሆን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ በማድረግ ለላቀ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ይጠበቃል፡፡ ነእፓ በዋነኛነት ከሚከተለው የለዘብተኛ ሊበራል ርዕዮተ ዓለም በተጨማሪ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሶሻል ዴሞክራትን ጨምሮ ሌሎች ርዕዮተ-ዓለማዊ አስተሳሰቦችን መሰረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ርዕዮተ-ዓለምን በተመለከተ ፓርቲያችን የሚከተለው ይህ አሰራር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከነገሰው በአንድ ርዕዮተ-ዓለም የመታጠር ጠባብ የፖለቲካ አረዳድ ወጣ ባለ መንገድ ከሊበራል አስተሳሰብ ጋር የማይጋጩ፣ የሀገራችንን የእድገት ደረጃ ታሳቢ ባደረገ መንገድ ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የሚያግዙ ሰፊ የፖሊሲ አማራጮችን ለማሰብ ይረዳል ተብሎ ይታመናል፡፡

 1. የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ከዚህ መሰረታዊ እምነት በመነሳት በዜጎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የህግ ዋስትናና ከለላ ያገኛሉ፣ ዜጎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የተጎናፀፏቸው መሰረታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ ይደረጋል፣
 2. ኢትዮጵያውያን የዘር፣ የብሄር/ብሄረሰብ፣ የሀይማኖት፣ የጾታ፣ የቋንቋ፣ የአካባቢ፣ የፖለቲካ አመለካከት ወዘተ ልዩነት ሳይደረግባቸው በፈለጉበት አካባቢ የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመስራትና ሀብት የማፍራት መብታቸው በተሟላ ሁኔታ እንዲከበር ይደረጋል፣
 3. መላው ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የደረጃ ልዩነት ሳይደረግባቸው፣ ስለ አገራቸው እኩል የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ህጎችና አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 4. ዜጎች በሚፈልጉት መልኩ የመደራጀት፤ ሀሳባቸውን የመግለፅ፣ የመፃፍ፣ የመቃወም መብታቸው ሳይሸራረፍ እንዲከበር ይደረጋል፣
 5. ዜጎች የአካልና የስነ-ልቦና ደህንነታቸው የህግ ከለላ ያገኛል፣ በህግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ድርጊት በመሳተፍ ምክንያት በፍርድ ቤት ውሳኔ ካልሆነ በስተቀር ህይወትና ንብረታቸው ይጠበቃል፣ ዜጎች ከፍትህ ስርዓት ውጪ ሊያዙ ብሎም ክስ ሳይቀርብባቸውና ሳይፈረድባቸው ፈጽሞ እንዳይታሰሩ፣ ኢ-ሰብዓዊ እና ክብርን ከሚያጎድል አያያዝ እና ቅጣት እንዲጠበቁ ይደረጋል፣
 6. ዜጎች በኃይል ተገደው ማንኛውንም ስራ እንዲሰሩ ወይም ግዴታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ አሰራር አይኖርም፣ 7
 7. ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊና ዴመክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች/ብሄረሰቦች፣ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ ባህሎች፣ ወጎችና ልማዶች፣ ኃማኖቶችና ማህበራዊ እሴቶች ያሏቸው ህዝቦች መኖሪያ ናት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ብዝሃ ህይወት፣ መልክአ ምድር፣ የአየር ጸባይና የአኗኗር ዘይቤዎች ላይ የተመሰረተ የማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ብዝሀነት ያሏት ሀገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘረጋ የመንግስት አወቃቀር እነዚህን የሀገራችንና የህዝባችንን ተፈጥሯዊ ልዩነቶችና ብዝሀነት ታሳቢ ያደረገ፣ በአንድነት ውስጥ ልዩነትን ማስተናገድ የሚያስችል፣ በመፈቃቀድ፣ በመከባበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆን ይኖርበታል፡፡

ነእፓ ለዚህ ዓላማው እውን መሆን የተሻለው የመንግስት አወቃቀር የፌደራል ስርአት ነው ብሎ ያምናል፡፡ እውነተኛ የፌደራል መንግስት አወቃቀር ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በስምምነት በመከባበር ተፈቃቅደው ለመኖር የሚያስችል ምቹ አስተዳደራዊ ስርአት ይፈጥራል፡፡ የሚገነባው የፌደራል ስርአት የአስተዳደር ምቹነትን፣ የህዝብ ፍላጎትን፣ ቋንቋና ባህልን፣ መልከዓ-ምድርንና ሌሎች የጋራ እሴቶችን ታሳቢ ያደረገ ይሆናል፡፡

ፓርቲያችን የሚከተለው የመንግስት ስርዓት ፕሬዚዳንታዊ ይሆናል፡፡ ፕሬዝደንቱ (ርዕሰ ብሄር) በቀጥታ በህዝብ የሚመረጥ ሲሆን ለአምስት ዓመታት ያገለግላል፡፡ አንድ ፕሬዝደንት ለሁለት ዙር መወዳደር ይችላል፡፡

ሕገ-መንግስት የዜጎችን መብቶችና ግዴታዎች እንዲሁም የመንግስትን አወቃቀርና አሰራር የሚወስኑ መሰረታዊ ህጎችና መርሆችን የሚይዝ የህግ እና የፖለቲካ ሰነድ ሲሆን በአንድ ሀገር ውስጥ የሚወጡ ህጎች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ፖሊሲዎች ወዘተ መነሻ ነው፡፡ሕገ-መንግስት መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የውጭ ግንኙነት መርሆችን የሚይዝ ለአንድ ሀገር ሰላምና ብልጽግ እንዲሁም ለዜጎች ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ነጻነት፣ እኩልነትና ፍትህ ዋስትና የሚሰጥ የዜጎች የመግባቢያ ሰነድ ነው፡፡ሕገ-መንግስት እንደ ስሙ የሀገርና የመንግስት ህግ ይሆን ዘንድ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ተቀባይነት ያለው፣ ግልጽና የማያሻማ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገራችንን ሕገ መንግስት ስንመለከተው መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ በመሆኑም ነእፓ በስራ ላይ ያለው የሀገራችን ሕገ-መንግስት የሚከተሉትን ነጥቦች ከግምት ዉስጥ በማስገባት መሻሻል አለበት ብሎ ያምናል፡፡

 1. ሕገ-መንግስቱ የሀገራችንን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያስከብር፣ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን የሚያስጠብቅና ሀገራችን ካለችበት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገትና አስከፊ ድህነት በፍጥነት እንድትላቀቅ በሚያስችል መልኩ ሊቃኝ ይገባል፣
 2. የዜጎቻችንን ሰላምና ደህንነት የሚሸረሽሩ፣ መገንጠልና መለያየትን የሚጋብዙ አንቀጾች ብሄራዊ መግባባትን፣ አብሮነትና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊሻሻሉ ይገባል፣
 3. የሕገ-መንግስት አንዱ ባህሪ ለረዥም ጊዜ ማገልገል መቻሉ ነው፡፡በመሆኑም ከሀገራችን የእድገት ደረጃ ጋር በየጊዜው ሊቀየሩ የሚገቡ ድንጋጌዎችን በሕገ-መንግስት ውስጥ ማካተት ህገ-መንግስቱ ወሳኝ የሆኑ ሀገራዊ ለውጦችን ማስተናገድ እንዳይችል በማሰር በአፈጻጸም ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም በየጊዜው ሊቀየሩ የሚገባቸውን አንቀጾች ከህገ-መንግስቱ ማውጣት ያስፈልጋል፣
 4. ሕገ መንግስት የአንድ ሀገር ዜጎች የጋራ ሰነድ በመሆኑ የአብዛኛውን ህብረተሰብና የፖለቲካ አስተሳሰብ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን እስከ ዛሬ በስራ ላይ የዋሉ ሕገ-መንግስቶች በጊዜው የነበሩ መንግስታት የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለምና የፖለቲካ ፕሮግራም ቅጅ ስለነበሩ ፓርቲ እና መንግስትን መለየት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በስራ ላይ ያለው ሕገ-መንግስተ ከገዥው ፓርቲ ርዕዮተ-ዓለምና የፖለቲካ ፕሮግራም ተለይቶ በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን አስተሳሰብና ፕሮግራም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ሊሻሻል ይገባል፣
 5. ቋንቋ፣ ባንዲራ፣ የክልሎች አመሰራረትና ወሰን የመሰሉ አሻሚና አላስፈላጊ ልዩነቶችና ግጭቶችን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ህገ-መንግስቱ ግልጽና የማያሻማ መልስ ሊሰጥ በሚችል መልኩ ሊስተካከል ይገባል፣

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች/ብሄረሰቦች፣ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ ባህሎች፣ ወጎችና ልማዶች፣ ኃማኖቶችና ማህበራዊ እሴቶች ያሏቸው ህዝቦች መኖሪያ ናት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ብዝሃ ህይወት፣ መልክአ ምድር፣ የአየር ጸባይና የአኗኗር ዘይቤዎች ላይ የተመሰረተ የማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ብዝሀነት ያሏት ሀገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘረጋ የመንግስት አወቃቀር እነዚህን የሀገራችንና የህዝባችንን ተፈጥሯዊ ልዩነቶችና ብዝሀነት ታሳቢ ያደረገ፣ በአንድነት ውስጥ ልዩነትን ማስተናገድ የሚያስችል፣ በመፈቃቀድ፣ በመከባበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆን ይኖርበታል፡፡

ነእፓ ለዚህ ዓላማው እውን መሆን የተሻለው የመንግስት አወቃቀር የፌደራል ስርአት ነው ብሎ ያምናል፡፡ እውነተኛ የፌደራል መንግስት አወቃቀር ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በስምምነት በመከባበር ተፈቃቅደው ለመኖር የሚያስችል ምቹ አስተዳደራዊ ስርአት ይፈጥራል፡፡ የሚገነባው የፌደራል ስርአት የአስተዳደር ምቹነትን፣ የህዝብ ፍላጎትን፣ ቋንቋና ባህልን፣ መልከዓ-ምድርንና ሌሎች የጋራ እሴቶችን ታሳቢ ያደረገ ይሆናል፡፡

1.6.1 የመንግስት የስራ ቋንቋ 

አማርኛና ኦሮምኛ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ ይሆናሉ፡፡ የፌደራል መንግስቱ አካል የሆኑት የክልል መስተዳድሮች በክልሉ ውስጥ በስፋት ከሚነገሩ ቋንቋዎች ውስጥ አንድ ወይም ከአንድ በላይ ቋንቋዎች የክልል መስተዳድሩ የስራ ቋንቋ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡

1.7.1 የሀገር መከላከያ ኃይል

 1. ለህዝብና በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ታማኝ የሆነ፣ ለሀገሪቱ ህገ-መንግስት ዘብ የሚቆም፣ ሀገራችንን ከማናቸውም አይነት የውስጥና የውጭ ጥቃት የሚከላከል የመከላከያ ኃይል ይገነባል፣
 2. የሀገር መከላከያ ኃይል ዋነኛ ተልዕኮ ሀገርና ህዝብን መጠበቅ፣ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት ማስከበር ይሆናል፣
 3. የሀገራችን ምጣኔ ሀብት በሚፈቅደው መጠን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ የመከላከያ ኃይል ይገነባል፣
 4. የመከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራር ስብጥር ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያማከለ እንዲሆን ይደረጋል፣ የሀገር መከላከያ ኃይላችን የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አመኔታ፣ ድጋፍ እና ተቀባይነት ማግኘት ይችል ዘንድ ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ይደረጋል፣
 5. የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሳይሆኑ፣ ተጠሪነታቸው በህዝብ ለሚመረጥ መንግስት ብቻ ይሆናል፣
 6. የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለጎረቤት ሀገሮች፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላም እና መረጋጋት ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችንና ህጎችን በጠበቀ ሁኔታ ተሳትፎ ሊያደርግ ይችላል፣
 7. የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራር ለሀገርና ለህዝብ ያላቸውን ውለታ ታሳቢ ያደረገ ልዩ የጉዳትና የህይወት ካሳ ይከፈላል፣ ሀገራዊ ግዳጅ በመወጣት ላይ ሳሉ ለሚሰዉ የሰራዊቱ አባላት ቤተሰቦች መንግስት ተገቢውን እንክብካቤና ድጋፍ ያደርጋል፣
 8. የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና ልዩ ልዩ ተቋማት በአስቸኳይና ድንገተኛ አደጋ ወቅት መንግስት ለሚያካሂደው የነፍስ አድን ዘመቻ በቂ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

 

1.7.2 የፖሊስና ደህንነት ኃይል

 1. ሙያዊ ብቃት ያለው፣ በስነ-ምግባር የታነፀ፣ ህግ የሚያከብርና የሚያስከብር፣ ከማናቸውም ዓይነት ወገንተኝነት የፀዳ ለህገ-መንግስቱ ታማኝ የፖሊስ ኃይል በፌደራልና በክልል ደረጃ ይገነባል፣
 2. የፖሊስ ሰራዊቱን ገለልተኝነት ለመጠበቅና ለአሰራር አመች ይሆን ዘንድ፣ የፖሊስ ሰራዊት አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይሆኑም፣
 3. በየደረጃው ያለው የፖሊስ ሰራዊት ተቋማት ሁሉንም የህብረተስብ ክፍል የሚወክሉ እንዲሆንና ዋነኛ ተልዕኮውም በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጣ ተቋም እንዲሆን ይደረጋል፣
 4. የደህንነት ተቋሙ የሀገርንና የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ የሚዋቀር ሲሆን ዋና ዓላማው ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ስጋቶችንና ሀይሎችን ቀድሞ በመለየት የህግ የበላይነትና የህዝብን ሰላም ማስከበር ነው፡፡
 5. የሀገር ደህንነት ተቋም የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ባልሆኑ አባላትና አመራሮች የተደራጀ፣ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት የማይንጸባረቅበት ተቋም እንዲሆን ይደረጋል፡፡