ፕሮግራሞቻችን

ስለ ፕሮግራሞቻችን በመረዳት ስለ ፓርቲያችን እንቅስቃሴዎች ይወቁ

በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተጀመረው የኢንዱስትሪ አብዮት በየምዕተ ዓመቱ ፍጥነቱን እየጨመረና አድማሱን  እያሰፋ አብዛኛውን የዓለም ሀገራት ያካተተ ሲሆን በዚህም አፍሪካን ጨምሮ ብዛት ያለው የዓለማችን ህዝብ የኑሮ ደረጃ  እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡የኢንዱስትሪ አብዮቱን ያቀጣጠለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት  በሀገሮችና በሰዎች ላይ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ በአንድ በኩል በሀገሮች፣ በህብረተሰብ፣ በድርጅቶችና በግለሰቦች መካከል ያለውን ርቀት በእጅጉ እንዲቀንስ፣ ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲስፋፋ፣ የዓለም የጤና  ደረጃ ከፍ እንዲል፣ አማካኝ የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር፣ የትምህርት ተሳትፎ እንዲያድግ፣ ጎጂ ባህሎችና እምነቶች  እንዲቀንሱ፣ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያድግ እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ሚና ተጫውቷል፡፡ በሌላ  በኩል በሀገሮችና በዜጎች መካከል የሀብትና የገቢ ልዩነት እንዲሰፋ፣ አካባቢ እንዲበከልና እንዲጎሳቆል፣ አውዳሚ ግጭቶችና ጦርነቶች እንዲበራከቱ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እንዲባባሱ፣ ግለኝነት እንዲገን፣ ያልተመጣጠነ የህዝብ  እድገትና ፍልሰት እንዲበራከት፣ ብሄርተኝነት እንዲስፋፋ፣ የቤተሰብና ማህበረሰብ መስተጋብርና ግንኙነት እንዲላላ፣  ስራ አጥነት እንዲጨምርና ወንጀል እንዲበራከት፣ ተደጋጋሚ የገንዘብና የምጣኔ ሀብት ቀውስ እንዲፈጠር . . .ወዘተ  ምክንያት ሆኗል፡፡ በአፍሪካ፣ አስያ፣ ደቡብ አሜሪካና የበለጸጉ በሚባሉ የአውሮፓና የአሜሪካ ሀገሮች ሳይቀር አስከፊ ድህነት ነግሷል፡፡  የዓለማችን ግማሽ የሚሆነው ሀብት ከዓለም ህዝብ አንድ ከመቶ በማይበልጡ ባለሀብቶች ቁጥጥር  ስር ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ታዳጊ ሀገራት ከጠቅላላው ዜጎች አንድ ከመቶ የማይበልጡ ባለሀብቶች  የየሀገራቱን 90 ከመቶ በላይ ሀብት ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡

ሉላዊነት (Globalization) በፍጥነት እያደገ በሚሄድበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን በሀገራችን የሚስተዋሉ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችና ተግዳሮቶች የተወሰኑት ዓለም ዓቀፍ ገጽታ ሲኖራቸው ቀሪዎቹ ሀገር በቀል እና የሀገራችን የፖለቲካና ማህበራዊ ታሪክ፣ አስተሳሰብና ግንኙነት የወለዷቸው ናቸው፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)የሀገራችን እና የህዝባችን ችግሮች ምንጭ በዋናነት ፖለቲካዊ እንደሆነ እና መፍትሄውም በአብዛኛው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እንደሆነ ያምናል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ አግላይ የፖለቲካ ስርዓት፣ ማኅበራዊ ፍትህ መጥፋት፣ አድሎ፣ ወገንተኛነት፣ ብሄርንና እምነትን መሰረት ያደረጉ ልምዶችና አሰራሮች የሀገራችን የፖለቲካ ስርዓት መገለጫዎች ሆነው ብዙ ዘመናት አልፈዋል፡፡ የዘር፣ የጎሳና የኃይማኖት ብሄርተኝነት ህዝባችንን ከፋፍሎ አንድነታችንን አላልቶታል፡፡ ለታሪካችን ያለን ቦታና አረዳድ እጅግ የተራራቀ ሲሆን ታሪካዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ልዩነቶቻችን እየሰፉ መጥተዋል፡፡ በታሪካዊ ጉዳዮች ዙርያ ገንቢ ያልሆኑ ክርክሮች ተበራክተው የመላው ህዝባችን መሰረታዊ ችግር በሆኑት ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ረሀብ፣ ስደት ወዘተ ላይ በርትተን እንዳንሰራ ኃይላችንን ከፋፍሎታል፡፡

ነጻና ገለልተኛ የፍትህ ስርዓት መጥፋት፣ ስራ አጥነትና ድህነት፣ የመሰረተ ልማት እጥረት፣ ማህበራዊ ቀውስ፣ የሀገርና የህዝብ ፍቅር መሸርሸር፣ በዜጎች መካከል በመተማመን ፈንታ ጥርጣሬ መንገስ ከሀገራችን አንኳር ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎት፣ በቂ ትራንስፖርትና መገናኛ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የህዝብ አስተዳደር የሀገራችን ህዝብ ህልም እና ምኞት መሆናቸው ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች መካከል የትምህርት፣ ጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች ሽፋን ዝቅተኛ ሲሆን ኢ-ፍትሀዊ ስርጭቱ እየሰፋ መጥቷል፡፡ ዓለም 4ኛ ትውልድ የኢንዱስትሪ እድገት ላይ በደረሰበት ዘመን የሀገራችን ኢኮኖሚ በዝናብ ላይ የተመሰረተ ዝቅተኛ ግብርና እና ደካማ የአምራች ኢንዱስትሪ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

የፓለቲካ ፕሮግራም

የሊበራል አስተሳሰብን ከሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ጋር አዋዶ ነባራዊ እና ተጨባጭ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እውነታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘብተኛ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም ይከተላ

 

ያንብቡ

የኢኮኖሚ ፕሮግራም

በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያለው ኢኮኖሚ ለአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ያለው ድርሻ ከግብርናው ዘርፍ በልጧል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና እና የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ያለው ድርሻ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል

ያንብቡ

ማህበራዊ ፕሮግራም

የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ከሚያሰፈልጉ ግብዓቶች ዋነኛው ነው፡፡ የተማረ የሰው ኃይል ውስን የተፈጥሮ ሀብትን አቀናብሮ ፈጣንና ዘላቂ ልማት፣ ተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓትና አስተማማኝ ሰላም፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወዘተ ለመገንባት የማይተካ ድርሻ አለው

ያንብቡ

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

የሀገራችን  የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስታራቴጂ ዋነኛ ግብ በሀገር ውስጥ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ  እቅዶችን ለማሳካት የሚደረውገን ጥረት ማገዝ ነው። የዚንም አላም ግብ ለመምታት እንዲያስችል ነ.እ.ፓ የተለያዩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስታራቴጂዎችን በምንደፍ ይንቀሳቀሳል።

ያንብቡ