ማህበራዊ ፕሮግራም

የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ከሚያሰፈልጉ ግብዓቶች ዋነኛው ነው፡፡ የተማረ የሰው ኃይል ውስን የተፈጥሮ ሀብትን አቀናብሮ ፈጣንና ዘላቂ ልማት፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓትና አስተማማኝ ሰላም፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወዘተ ለመገንባት የማይተካ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ዘርፈ ብዙ እና ውስብስበ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችና ተግዳሮቶች ላላቸው ሀገሮች፣ ካሉበት የድህነት አዙሪት ለመላቀቅ ትምህርትና ስልጠና ቁልፍ የለውጥ መሳሪያ ናቸው፡፡ የትኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ፤ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎት ሰጭ የሰለጠነ እና የበቃ የሰው ኃይል ይሻል፡፡ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት፣ መልካም አስተዳደር፣ ነጻና ግልጽ ምርጫ፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር፣ ፖለቲካዊ መቻቻል ወዘተ ስልጡን ማህበረሰብ ይፈልጋሉ፡፡ ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር፣ ለሰው ልጅ ነጻነት፣ ደህንነትና እኩልነት ዘብ የሚቆም፣ ለፍትሕና ለሠላም መከበር የሚታገል፣ በአካልና በሥነ-ምግባር የታነጸ፣ ለሀገርና ለህዝብ ፍቅር ያለው፣ ሁለንተናዊ ስብዕና የተላበሰ ትውልድ የማፍራት ስራ ከትምህርት ቤት ይጀምራል፡፡ በቂ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በንድፍ ሀሳብና በተሞክሮ የተረጋገጠ፣ የሀገራችንን የትምህርትና ስልጠና ታሪክ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የእድገት ደረጃ፣ የህዝቦቿን ወግ፣ ባህልና ብዝሀነት ወዘተ ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ ዓለም ዓቀፍ የስነ-ትምህርት ደረጃዎችንና እመርታዎችን ያገናዘበ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና ፕሮግራም ያስፈልጋል፡፡

የትምህርት ስርዓታችን በእውቀት የተካኑ፣ በጥልቀት ማስተንተንና መፍጠር የሚችሉ፣ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የአመራር ብቃት ያላቸው፣ በመልካም ስነ ምግባር እና ሰብዓዊነት የተሞሉ፣ የሀገር እና ህዝብ ፍቅር ያላቸው፣ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እና ለሀገራቸው ዕድገት አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ወጣቶችን ማፍራት እንዲችል ተደርጎ ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ በሰው ኃይል ልማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት በየትኛውም ዘርፍ ላይ ከሚፈስ መዋዕለ-ንዋይ እጅግ አዋጭና ለግለሰብ፣ ማህበረሰብና ለሀገር ዕድገት ተወዳዳሪ የሌለው አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችል ነው፡፡ የሀገራችን የትምህርትና ስልጠና ሴክተር በበርካታ ውስብስብ ችግሮችና ተግዳሮቶች የተከበበ ነው፡፡ የሀገራችን የትምህርት ዘርፍ ችግሮች ሲዳሰሱ የትምህርት ስርጭትና ተደራሽነት፣ ጥራት፣ አግባብነትና ፍትሐዊነት ጎልተው ይታያሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች ከትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ከሰው ኃይል ልማት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚከተሉት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

 1. የዘመናችንን መልካም አጋጣሚዎች በተሻለ መንገድ ለመጠቀምና እና ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚችል ትውልድ ማፍራት የሚችል የትምህርት ስርዓት ይዘጋጃል፣ የተማሪዎችን የችግር ፈችነት አቅም ከፍ የሚያደርጉ የትምህርት ፕሮግራሞች ይቀረጻሉ፣
 2. የትምህርት ስርዓታችን አህጉራዊና ዓለም-ዓቀፍ ተወዳዳሪነታችንን ከፍ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ይቀረጻል፣
 3. ቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያ ደረጃ፣ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ፣ የቴክኒክና ሙያ ስርዓተ ትምህርትና የማስተማር ዘዴዎች እንዲሻሻሉ ይደረጋል፣
 4. የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ተፈትሾ ከሀገራችን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ጋር በተናበበ መልኩ ይቀረጻል፣
 5. የትምህርት ሴክተሩ ቁልፍ ግብዓት ለሆኑት መምህራን ልዩ ትኩረት በመስጠት የመምህርነት ሙያ የተከበረና በህብረተሰቡ ውስጥ የላቀ ሙያ እንዲሆን ለመምህራን ልዩ ልዩ ድጋፎችና ማበረታቻ ይደረጋል፣
 6. የሞራል፣ የስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋ ትምህርቶች በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ በሚገባ ተዋህደው ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ ለተማሪዎች በተጠናከረ መንገድ እንዲሰጡ ይደረጋል፣
 7. ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ (STEM) ትምህርቶች ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ አራቱ የትምህርት ዓይነቶች ዓለም-አቀፍ ተሞክሮን በመዳሰስ በተዋሀደ እና በተቀናጀ መንገድ የሚሰጡበት ስርዓተትምህርት ይቀረጻል፣
 8. ዜጎች ቢያንስ የአስር ዓመት አጠቃላይ መሰረታዊ ትምህርት እንዲማሩ የመንግስትና ቤተሰብ ግዴታ ይሆናል፣
 9. ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ይደረጋል፣
 10. ትምህርት ቤቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት አሰጣጥ አቅም እንዲኖራቸው ለማስቻል የድምጽ እና የምስል ክምችት አንዲኖራቸው፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቂ ድጋፍ ይሰጣል፣
 11. በትምህርት ዘርፍ ለተሰማሩ የግል ባለሀብቶች ልዩ ልዩ ማበረታቻና ድጋፍ ይደረጋል፣ የመንግስትና የግል የትምህርት ተቋማት የቁጥጥር እና ግምገማ ስርዓት ተመሳሳይ እንዲሆን የሚደረግ ሲሆን፣ በግል የትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ ትኩረት እና አላስፈላጊ ጫና የሚፈጥር ብልሹ አሰራር እንዲቀር ይደረጋል፣
 12. የትምህርት ተቋማትን ከፖለቲካ ነጻ በማድረግ መምህራንና ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ይደረጋል፡፡ የትምህርት ተቋማት ከመንግስት እና ከህብረተሰቡ ጋር በመረዳዳት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ስርዓት ይዘረጋል፣
 13. በትምህርት ሽፋንና ጥራት ዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ የአርብቶ-አደርና ከፊል አርብቶ-አደር አካባቢዎች ልዩ ድጋፍ በማድረግ የሀገራችን የትምህርት ስርጭት ፍትሀዊ እንዲሆን ይደረጋል፣
 14. የቅድመ-መደበኛ፣ የመጀመሪያ ደረጃ፣ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና የከፍተኛ ትምህርት ቅበላ፣ ጥራት፣ ሽፋን ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገሮች የተሻለ እንዲሆን ይደረጋል፣
 15. ተማሪዎች ከመጀመሪያ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲሸጋገሩ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ከፍተኛ እጥረት ለመቀነስ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፣
 16. በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ከግምት ውስጥ ያስገቡ፣ የጎልማሶችን ምርታማነት ሊያሳድግ የሚችል፣ ከጐልማሶች ሕይወት ጋር በቀጥታ የሚገናኙ እና የጐልማሶችን ፍላጐት መነሻ ያደረጉ የክህሎት ሥልጠናዎች እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡

"ትምህርት-ተኮር ብሄራዊ የልማት ስትራቴጂ"

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ለትምህርትና አጠቃላይ የሰው ኃይል ልማት የሚሰጠው ትኩረት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ትምህርትና ስልጠና እንደ ሌሎች የልማት ዘርፎች እንደ አንድ ሴክተር ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን የአጠቃላይ ሀገር አቀፍ ልማት መሰረት ሆኖ የሚያገለግል ቁልፍ ዘርፍ ነው፡፡ ነእፓ ትምህርት ለሀገራችንና አጠቃላይ ለሰው ልጆች ስልጣኔ የተጫወተውን ቁልፍ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባትና በልማት ወደፊት የተራመዱ የዓለም ሀገራትን “ሚስጥረእድገት” በጥልቀት በመመርመር “ትምህርት-መር ብሄራዊ የልማት ስትራቴጂ” ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት እና ብልጽግ ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ እምነት በመነሳት ትምህርትና ስልጠናን ጨምሮ ሌሎች የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራሞች የነእፓ ሀገራዊ የልማት ፍልስፍና እና ፖሊሲዎች የመሰረት ድንጋይ ሆነው ለሚቀጥሉት በርካታ አመታት ያገለግላሉ፡፡ ይህ ትምህርት-መር የልማት ስትራቴጂ ሀገራችንን በአጭር ግዜ ውስጥ ካለችበት አስከፊ ድህነት አላቆ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች መሀል ለማስገባት በሂደትም በዓለም የበለጸጉ አገሮች ክበብ ውስጥ ቦታ እንድትይዝ ዋነኛው የፖሊሲ ማዕቀፍ ሆኖ ያገለግላል፡ ፡ በዚህም መሰረት የትምህርት ዘርፍ የሀገራችን ሁለንተናዊ ልማት እና ብልጽግና የመሰረት ድንጋይ በማድረግ ሁሉም የመንግስት የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የሰው ኃይል ልማትን ያማከሉ ይሆናሉ፡፡

በሀገራችን ከተንሰራፉ ማህበራዊ ቀውሶች አንዱ ጤና ነው፡፡ የሀገራችን የጤና ተቋማት በብዛት፣ በጥራትና በአደረጃጀት ኋላ ቀር ናቸው፡፡ የመንግስትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት ብዛት ከሀገራችን የህዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ዜጎች በቂ የህክምና አገልግሎት በአካባቢያቸው ማግኘት አይችሉም፡፡ ከዚህ ባሻገር የጤና ተቋማት ስርጭት ፍትሀዊነት የጎደለውና በጥቂት የክልል ዋና ከተሞች ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች ብዛት፣ የህክምና መሳሪያዎችና የመድሀኒት አቅርቦት ከፍተኛ እጥረት የጤና ዘርፉን ችግሮች ይበልጥ ከባድና የተወሳሰበ አድርጎታል፡፡ ነእፓ የሀገራችን የጤና ዘርፍ ያሉበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማስወገድና ህዝባችን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል የሚከተሉትን የጤና ፕሮግራሞች ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

 1. የጤናን ሁለተናዊ እሳቤን መሠረት ባደረገ መልኩ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ፖሊሲ ይቀረፃል፣
 2. ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመገንባት የጤናው ሴክተር ከሌሎች ሴክተሮች ጋር እንዲቀናጅ ይደረጋል፡፡ በመሆኑም ሌሎች ለጤናው ዘርፍ ልማት በቀጥታና በተዘዋዋሪ አስተዋፅዖ ያላቸው ሴክተሮች፤ ትምህርት፣ ውሃ፣ ግብርና፣ ድህነት ቅነሳ፣ ፋይናንስና ኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ፣ መንገድና ትራንስፖርት፣ ብዙሀን መገናኛ የመሳሰሉትን ከጤናው ሴክተር ጋር በተቀናጀ መልኩ የሚሰሩበት ስርዓት ይዘጋጃል፣
 3. በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ልዩ ትኩረት የሚሰጥ፣ ተገቢውን ህክምና በወቅቱ ማቅረብ የሚችል፣ ህሙማን ከህመማቸው አገግመው ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንዲገቡ የሚያደርግ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ተቀርጾ ተግባራዊ ይደረጋል፣
 4. ተላላፊ በሽታዎች በአብዛኛው የህብረተሰባችን ክፍል ዋነኛ የጤና ቀውስ ብሎም የሞት መንስኤ ናቸው፡፡ ተላላፊ በሽታንና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል የማህበረሰቡን ተሳትፎና ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ዘላቂ ስትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ ይሆናል፣
 5. በሀገራችን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍተዋል፡፡ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብና የስኳር ህመም፣ ካንሰርና ሌሎች በሽታዎች በጤናው ሴክተር ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከሚሞቱት ሰዎች ውስጥ ከ50% በላይ የሚሆኑት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም ተላላፈ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም የፖሊሲ ማዕቀፍ ተቀርጾ ስራ ላይ ይውላል፣
 6. ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ የማህበረሰብ ልማድ እንዲሆን መንግስት ድጋፍና ማበረታቻ የሚሰጥበት አግባብ ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል፣
 7. የአዕምሮ ጤናው ያልተጠበቀ ማህበረሰብ ጤናው የተሟላ ሊሆን አይችልም፣ ስኬታማ ህይወትን መምራትም አይችልም፡፡ የአዕምሮ ጤና ችግር በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በስፋት የሚታይ ቢሆንም በመስኩ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት ከፍተኛ የተደራሽነትና ጥራት ውስንነት ይታይበታል፡፡ የአዕምሮ ጤና አገልግሎት ከሌሎች የጤና አገልግሎት በተቀናጀ ሁኔታ ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል፣
 8. በሀገራችን የእናቶችና የህፃናት ሞት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ዛሬም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል የጨቅላ ህጻናትና የእናቶች ሞት ከሚከሰትባቸው ሀገራት አንዷ ነች፡፡ የሕፃናት፣ አፍላ ወጣቶችና እናቶችን ጤንነትና ደህንነት በተሟላ መልኩ የሚያስጠብቅ ስትራቴጂ ይዘጋጃል፣
 9. የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለተለያዩ ተላላፊ እና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ሞት መንስኤዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሀገራችን ያለውን የስርዓተ-ምግብ ሁኔታ ለማሻሻል የጤናው ሴክተር ከሌሎች ሴክተሮች ጋር በተቀናጀ መልኩ የሚሰራበት ስርዓት ተቀርጾ ተግባራዊ ይደረጋል፣
 10. ለጤና ጠንቅ የሆኑ እፆች በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡ የአልኮል መጠጦች፣ ትምባሆና አደንዛዥ እፆች የመሳሰሉ ጎጂ ሱሶችን ለማስቆም ጠንካራ ፖሊሲ በመንደፍ የህብረተሰባችን በተለይም የወጣቱ ጤንነትና ደህንነት እንዲጠበቅ ይደረጋል፣
 11. ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት የጤና ባለሙያ ብቃትና ስነ-ምግባር ቁልፍና የማይተካ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም በጥናት ላይ የተመሰረተና የሀገሪቱን የበሽታ ስርጭት ያገናዘበ የጤና ስርዓተ-ትምህርት እንዲቀረፅ ድጋፍ ይደርጋል፡፡ በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሥራ ላይ ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ተነድፈው ተፈጻሚ ይሆናሉ፣
 12. የጤና ባለሙያዎች የኑሮ ሁኔታ አለመመቻቸት ለህብረተሰቡ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የጤና ባለሙያውን ለመደገፍ የተለያዩ የማበረታቻ ፓኬጆች ተቀርጸው በስራ ላይ ይውላሉ፣
 13. ጠንካራ የጤና ባለሙያዎች ማህበር መኖር ሙያው የሚጠይቀውን የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም በተለያዩ የጤናና ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ የጤና ባለሙያዎች በማህበር እንዲደራጁና ሙያቸውን እንዲያዳብሩ አስተዳደራዊ ድጋፎች ይሰጣሉ፣
 14. መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል፣
 15. መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ማግኘት የሁሉም ዜጋ መብት ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም ዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግ አቅምን ያገናዘብ የጤና መድህን ሥርዓት ይዘረጋል፣ መንግስት ለጤናው ዘርፍ የሚያደርገው የበጀት ድጎማ ከፍ እንዲል ይደረጋል፣
 16. በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የግብዓት ችግር ለመቅረፍ መድሀኒትና ሌሎች የጤና ግብዓቶች በሀገር ውስጥ በጥራት እና በበቂ ሁኔታ እንዲመረቱ ማበረታቻ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የጤና ግብዓቶች አያያዝና ስርጭትን ዘመናዊና ያልተማከለ እንዲሆን የተሻሻሉ ሥርዓቶች ይዘረጋሉ፣
 17. የጤና ተቋማትን የመረጃ አያያዝ እና ትስስር ለማሻሻል፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ እና ለማዘመን ኢ-ሄልዝ (e-health) እና ሌሎች የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡
 18. በጤና መስክ ጥናትና ምርምር ማድረግ የተሻለ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ሥራዎችን ለመስራት ጉልህ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በጤና ላይ የሚሰሩ ጥናቶች እንዲስፋፋና የህብረተሰቡን የጤና ችግሮች ለመፍታት የሚያግዙ የፖሊሲ ግብዓት መሆን እንዲችሉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከሎች ጋር በጋራ የሚሰራበት ስርዓት ይዘጋጃል፣
 19. ጤናውና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር መንግስት፣ የሲቪክ ማህበራትና የግሉ ሴክተር በቅንጅት የሚሰሩባቸው መድረኮች ይመቻቻሉ፡፡

ውብ፣ ዘመናዊ፣ ምቹና ንጹህ ከተሞች እና አካባቢዎች ለዜጎች ሁለንተናዊ ህይወት እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ዜጎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን በተሳካ ሁኔታ ለመከወን እንዲችሉ ብሎም የአካልና የአዕምሮ ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ዘመናዊ እና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞች እንዲሁም በቂ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የመኖሪያ ቤቶች መገንባት ያስፈልጋል፡፡ የከተሞች እና ቤቶች ዲዛይንና ግንባታ የአንድን ማህበረሰብ ስልጣኔ ማሳያ እና የባህል መገለጫዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ለመኖሪያ፣ ለስራ፣ ለትምህርትና ለመዝናናት ምቹ ብሎም ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት በሚሰጥ መልኩ ከተሞችን መገንባትና ማስተዳደር ነእፓ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ፕሮግራሞች ውስጥ ነው፡፡

3.3.1 የከተማ ልማት

የሀገራችን የክትመት ምጣኔ 20% ያልዘለለ ሲሆን ይህም ከሰሀራ በታች ካሉ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ጋር እንኳ ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ በአንጻሩ አዲስ አበባን ጨምሮ አንዳንድ የክልል ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በ2010 በሀገራችን 971 ከተሞች የነበሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ100,000 (መቶ ሺህ) በላይ ህዝብ ያላቸው 17 ከተሞች እንዲሁም ከ2000 (ሁለት ሺህ) ህዝብ በላይ ነዋሪ ያላቸው 803 ከተሞች እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን የከተሞች ዕድገት አለመመጣጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው፡፡ ያልተመጣጠነ የከተሞች ዕድገት የከተሞች የመሠረተ-ልማት አቅርቦት እና አገልግሎት አሰጣጥ የተዛባ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

በመሆኑም ከህዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር የሚጣጣም፣ በጥናትና መረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ለነዋሪዎች በቂ እና ጥራት ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል የከተማ ልማት ፕሮግራም መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ የከተሞችን ዕድገት ከሚያዛቡ እና ጤናማ ዕድገት እንዳይኖር ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን ለመቀነስ የሚያስችል የተቀናጀ የከተማ ልማትና የገጠር ልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

3.3.2 የቤቶች ልማት

የመኖሪያ ቤት እጥረት በሀገራችን ከሚስተዋሉ ቁልፍ ማህበራዊ ችግሮች አንዱ ሲሆን በሀገራችን ካለው ፈጣን የህዝብ ቁጥር አንጻር ችግሩ በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በከተሞች አካባቢ ያለው የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ሰፊ ልዩነት ያለው ሲሆን ይህም በከተሞች ውስጥ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር እጅግ አባብሶታል፡፡ ሀገራችን ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች ባለው ከፍተኛ የቤት ችግር ሳቢያ በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩ ቤተሰቦች ቁጥር፣ ደባልነት እና ቤት የለሽነት /Homelesness/ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

ለመኖሪያ ቤት ችግር መስፋፋት የሚከተሉት ምክንያቶች በግምባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ፣

 • የተሳሳተ የመሬት ኪራይ አስተዳደር እና አሰራሩ የፈጠረው የመሬት አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን፣
 • ለቤት ግንባታ የሚሆን በቂ የፋይናንስ ምንጭ አለመኖር፣
 • ኃላፊነት በጎደላቸው የመሬት ነጋዴዎችና የመንግስት ባለስልጣናት በቅንጅት የሚደረግ ህገ-ወጥ የመሬት ቅርምት፣
 • ከመሬት ንግድ ወደ ፊት ትርፍ ለማግኘት ሰፊ የከተማ መሬት ጥቅም ላይ ሳይውል እንዲቆይ የሚፈቅድ ብልሹ አሰራር (Speculation)፣
 • ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የተንሰራፋው ከፍተኛ ሙስናና ህግ አልበኝነት፣
 • አቅምን ያላገናዘበ የቤት ስታንዳርድ እና ግልፅ የቤት ልማት ፖሊሲ አለመኖር፡፡

እነዚህንና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የመኖሪያ ቤትና ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚከተሉት ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

 1. የዜጎች የመኖሪያ ቤት ማግኘት ጉዳይ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያደርጉ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡ ይደረጋል፣
 2. መንግስት ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ከፍተኛ ሀብት ይመድባል፣
 3. የግል ባለሀብቶች በመኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲሳተፉ ማበረታቻ ይሰጣል፣
 4. መኖሪያ ቤት መገንባት/መግዛት የሚሹ ወገኖች ከገንዘብ ተቋማት የረዥም ጊዜ ብድር በአነስተኛ ዋጋ የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል፣
 5. የመኖሪያ አካባቢዎች በቂ እና ምቹ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች እንዲኖራቸው ይደረጋል፣
 6. በአነስተኛ ወጪ እና በቀላል ቴክኖሎጂ የሚገነቡ ቤቶች እንዲስፋፉ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 7. ውጤታማ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን ዕውን ለማድረግ የሚረዱ ጥናቶችን ለማካሄድና ዓለም-ዓቀፍ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም የሚረዱ መድረኮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ለማዘጋጀት የሚያግዝ አሰራር ይዘረጋል፡፡

ከሀገራችን ህዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት መሰረት እና ዋስትና ናቸው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ እና ተስፋ በዛሬዎቹ የሀገራችን ወጣቶች ይወሰናል፡፡ የሀገራችን አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና የሚወሰነው ዛሬ ለወጣቶቻችን በምንሰጠው ትኩረት፣ ወጣቶቻችንን ለማልማት በምንሰራው ስራና ለዚሁ በምናፈሰው ሀብት ነው፡፡ ወጣቶች እምቅ የማሰብ እና የመስራት ኃይል፣ ፍላጎት፣ ድፍረት፣ ስጋትን የመቀበል (Risk taking) ዝንባሌ ያላቸው ሲሆን እነዚህ የወጣትነት ባህሪያት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውሉ ከተደረገ ሀገርን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚዎች ይሆናሉ፡፡

በሀገራችን ታሪክ ወጣቶች በፖለቲካው ዘርፍ አምባገነን ስርዓቶችን በመታገል ለሀገር ትልቅ ውለታ ውለዋል፣ በኢኮኖሚው መስክ በገጠር እና በከተማ፣ በግብርና፣ በኢንደስትሪና በአገልግሎት ሰጭ መስኮች ተሰማርተው ወደር የማይገኝለት ስራ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የሀገራችን ወጣቶች ለከፋ ስራ አጥነትና ተያያዥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠው ለአስከፊ የህይወት ውጣ ውረድ ተዳርገዋል፡፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሀገራችንን ወጣቶች ዘርፈ ብዙና ጥልፍልፍ ችግሮች ለመቅረፍ ብሎም ወጣቶች ለሀገራችን ልማትና ብልጽግና ሁነኛ ሚና ይኖራቸው ዘንድ የሚከተሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ይከተላል፡፡

 1. ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ተቀርጸው ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 2. ወጣቶች በሀገራችን ዘላቂ ልማት፣አስተማማኝ ሰላም እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፣
 3. ወጣቶችን በአካልና በስነ-ልቦና እንዲታነጹ እና ከጎጂ ልማዶች እንዲጠበቁ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያና መዝናኛ ስፍራዎች እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፣
 4. ወጣቶች ተደራጅተው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ማስከበር ይችሉ ዘንድ በቂ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያግዝ አሰራር ይዘረጋል፣
 5. ወጣቶች በቂ ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ፣ የምርምርና የፈጠራ አቅማቸው እንዲዳብር መንግስት በቂ ሀብት ይመድባል፣ ወጣቶች ከፍተኛ የማንበብ ባህል እንዲያዳብሩ የፌደራልና የክልል መስተዳድር አካላት ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥሩ ይደረጋል፣
 6. ወጣቶች የዛሬዋ እና የነገዋ ኢትዮጵያ መምህራን፣ ሳይንቲስቶች፣ ሀኪሞች፣ ፖሊሶች፣ ወታደሮች፣ ስራ ፈጣሪዎችና ኢንቨስተሮች፣ ተመራማሪዎች፣ ፖለቲከኞችና የህዝብ አስተዳዳሪዎች፣ የጥበብ ሙያተኞች፣ . . . ናቸው፡፡ በመሆኑም የወጣቶች ልማት እና የሀገር ልማት የማይነጣጠሉና የተቆራኙ አድርጎ በመውሰድ ከፍተኛ የፖሊሲ ትኩረት ይሰጣል፣ በቂ መዋዕለ-ንዋይ ይመደባል፣
 7. የወጣቶችን ለበሽታ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚረዱ የወጣቶች ጤና እንክብካቤ እና ድጋፍ የሚደረግበት ስርዓት ይዘረጋል፣ ወጣቶች የስነ-ጾታ ግንዛቤያቸው ከፍ እንዲል በቂ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፣
 8. በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የሚኖሩ ወጣቶች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ መልካም ተሞክሮዎቻቸውን እንዲለዋወጡና የባህል መስተጋብር እንዲፈጥሩ ልዩ ልዩ መድረኮች ይዘጋጃሉ፣
 9. ወጣቶች የሀገርና የህዝብ ፍቅር እንዲኖራቸው፣ ሀገራዊ እሴቶቻችንን ጠብቀው እና ከጎጂ መጤ የባህል ተፅዕኖ ተጠብቀው መኖር እንዲችሉ አስፈላጊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

በሀገራችንም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ሴቶች እና ህጻናት በተለያዩ የተሳሳቱ ልማዶችና ጎጂ አስተሳሰቦች ምክንያት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ሲሸራረፉና ጥቅሞቻቸው ሲጓደሉ ማየት የተለመደ ክስተት ነው፡፡ የሴቶችና ህጻናት መብቶች ከአጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶች የማይነጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሴቶችና ህጻናት መብቶች የማይከበርበት ሀገር እና ማህበረሰብ ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚኖረው ግንዛቤና አተገባበር የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸጉ እና የተሻለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ሀገሮች ሳይቀር የሴቶችን መብት በማክበር እና የህጻናትን መብት ከመጠበቅ አንጻር ያላቸው ታሪክ የደበዘዘ ነው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሀ ሀገሮች ሴቶች ለጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ፤ ታዳጊ ህጻናት ለከፋ የጉልበት ብዝበዛ የተዳረጉ ናቸው፡፡

በእውቀትና በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ሴቶች እንደ እናት፣ እህት እና እንደ ልጅ ልዩ ትኩረትና እንክብካቤ ሊደረግላቸው፣ መብቶቻቸውን ከሚሸራርፉ ልማዶች፣ ጎጂ ባህሎችና አሰራሮች እንዲጠበቁ ተገቢ የህግ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት በአካል፣ በእውቀት፣ በስነ-ምግባር እና በስነ-ልቦና ተገንብተው የነገዋን ኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ ማበልጸግና ማስተዳደር ይችሉ ዘንድ ልዩ የፖሊሲ ትኩረት ይሻሉ፡፡

ፖለቲካዊ ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩ፣ ከአስተዳደራዊ መድሎ እንዲጠበቁ፣ ከጾታዊ ጥቃትና ኢ-ፍትሀዊ የጉልበት ብዝበዛ ከለላ እንዲያገኙ ልዩ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡ ነእፓ ለዘመናት ስር ሰደው የቆዩ ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ ልማዶች፣ ወጎችና አስተሳሰቦች በሴቶችና ህጻናት ላይ ያደረሱትን ዘርፈ ብዙ ጫናዎችና ተግዳሮቶች ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ የተቀናጀ የፖሊሲ እና የአሰራር ስርዓቶች እንዲዘረጉና ተግባራዊ እንዲሆኑ ሳያለሰልስ ይሰራል፡፡ የሴቶችና ህጻናት መብትና ጥቅሞችን ለማስከበር ከምንም በላይ የአመለካከት እና የአስተሳሰብ ለውጥ መኖር እንዳለበት የሚያምነው ነእፓ ከሴቶችና ህጻናት አንጻር የሚከተሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ይከተላል፡፡

ሴቶችና ህጻናትን በተመለከተ

 1. ሴቶችና ህጻናትን በተመለከተ በሀገር-ዓቀፍ፣ አህጉር-ዓቀፍ እና በዓለም-ዓቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ ህጎችና ስምምነቶች የሴቶችንና ህጻናትን መብቶች በሚያስጠብቅ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይሰራል፣
 2. በማዕከላዊ መንግስት እና በክልል መስተዳድር አካላት የሚወጡ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች የሴቶችና ህጻናትን መብቶችና ጥቅሞች በልዩ ሁኔታ የሚያከብሩና የሚያስከብሩ እንዲሆኑ ይደረጋል፣
 3. ሴቶችና ህጻናትን በተመለከተ የተሳሳቱና ጎጂ ልማዶች፣ አስተሳሰቦች፣ አሰራሮች ወዘተ ለመቀየርና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ፤
 4. የሴቶችንና ህጻናትን ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፍትሀዊ ተጠቃሚት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 5. በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ህገወጥ እና ኢ-ሞራላዊ ጥቃቶችና ትንኮሳዎች ሙሉ ለሙሉ ይቆሙ ዘንድ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ማዕቀፎች እንዲዘረጉ ይደረጋል፡፡

ሴቶችን በተመለከተ

 1. የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ የሚያሳድጉና የሴቶችን መጠነ ማቋረጥ (Drop out) የሚቀንሱ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ፣ ልዩ የማበረታቻ ድጋፎች የሚያገኙበት አሰራር ይዘረጋል፣
 2. ሴቶች በመንግስት፣ በግል፣ መንግስታዊ ባልሆኑ እና ዓለም-ዓቀፍ ድርጅቶች ተመጣጣኝ የስራ ዕድል እንዲያገኙ የሚያግዝ የህግ ማእቀፍና አሰራር ይዘረጋል፣ ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብታቸው እንዲከበር አስፈላጊ የህግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ ይደረጋል፣
 3. ሴቶች በቂ የወሊድ እረፍት ከሙሉ ክፍያ ጋር፣ እንዲሁም ተጨማሪ እረፍት ያለክፍያ እንዲያገኙ ይደረጋል፣
 4. በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች ከጾታዊ ትንኮሳ ተጠብቀው ትምህርታቸውን በነጻነት እና በትጋት መከታተል እንዲችሉ የሚያግዙ የሴቶች ትምህርት ቤቶች (የአንድ ጾታ ትምህርት ቤቶች) በመንግስት፣ በግሉ ሴክተርና በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲስፋፉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል፣
 5. በአብዛኛው የሀገራችን ህዝቦች ተቀባይነት የሌላቸው ጾታዊ መስተጋብሮች፣ የሴቶችን ሰብዓዊ ክብር የሚያረክሱ መጤ ወግና ባህሎች፣ ድርጊቶችና አሰራሮች እንዲወገዱ ይደረጋል፣
 6. ከቅድመ ትምህርት እስከ ከፍተኛ ትምህርት በሚዘጋጁ ስርዓተ-ትምህርቶች ውስጥ ስርዓተ-ጾታ በቂ ትኩረት እንዲያገኝና ጾታዊ መድሎን ሊፈጥሩ የሚችሉ የትምህርት ይዘቶች እንዲሻሻሉ ወይም ሙሉ ለሙሉ እንዲወገዱ ይደረጋል፣
 7. ሴቶች ተደራጅተው መብታቸውን እና ጥቅሞቻቸውን ያስከብሩ ዘንድ ልዩ ልዩ የሴቶች ማህበራት እና ድርጅቶች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት ወዘተ ማቋቋም እንዲችሉ ልዩ ድጋፍ ይደረጋል፣
 8. የሴቶች፣ የእናቶች እና የእህቶች ቀን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ በማድረግ ባለድርሻ አካላት እና ዜጎች ሴቶችን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት እንዲስተካከል የሚያግዙ አሰራሮች ይዘረጋሉ፣
 9. በተለይም የገጠሯን ሴት የኑሮ ጫና ሊቀንሱ፣ ማህበራዊ ሸክሟን ሊያቃልሉ እና ሰብዓዊ መብቶቿ ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ሊያደርጉ የሚችሉ አሰራሮች ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል፣
 10. ሰላምን፣ መቻቻልን እህትማማችነትን/ወንድማማችነትን በማስፈን ረገድ ሴቶች ያላቸውን ተፈጥሯዊ ክህሎትና ዝንባሌ እንዲጠቀሙ፣ ሴቶች በግጭት አፈታትና እርቅን በማውረድ ስራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ በማድረግ በሰላም ግንባታ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡

ህጻናትን በተመለከተ

 1. ህጻናት የስነ-ልቦናና አካላዊ ደህንነታቸው ተጠብቆላቸው ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችል የተቀናጀ የህጻናት ድጋፍና እንክብካቤ ፕሮግራሞች ይቀረጻሉ፣
 2. የህጻናት የነገ ህይወት የሚወሰነው ከምንም በላይ ዛሬ ላይ በሚያገኙት ትምህርትና እውቀት በመሆኑ፣ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል፣ በከተማም ይሁን በገጠር የሚኖሩ ህጻናት የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ስርዓት ይዘረጋል፣
 3. የህፃናት ጤና በተሟላ ሁኔታ እንዲጠበቅ፣ ከተለያዩ በሽታዎች የሚከላከሉ በቂ ክትባቶች በወቅቱና በአግባቡ እንዲያገኙ በሀገሪቱ የጤና ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል፣
 4. በሰው ሰራሽም ይሁን በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት የሚያጋጥማቸው ህጻናት ልዩ እንክብካቤ እንዲያገኙ፣ የአደጋ ተጋላጭነታቸው እንዲቀንስ ይደረጋል፣
 5. ለህጻናት የተሟላ አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ዕድገት እገዛ የሚያደርጉ በቂ የመጫወቻ እና መዝናኛ ቦታዎች ይኖሩ ዘንድ በከተሞች ፕላን ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል፣
 6. ህጻናት ለህገወጥ የጉልበት ብዝበዛ (Child labor) እንዳይዳረጉ የሚከላከል በቂ የህግ ከለላ እንዲኖር ይደረጋል፣ በዚህ ተግባር ላይ የሚሰማሩ አካላትን ለመቆጣጠርና ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችል ስርዓት ይዘረጋል፣
 7. የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ልምድ የሚቀስሙበትና ልምምድ የሚያደርጉበት መድረክ ይኖራቸው ዘንድ ጠንካራ ሀገር አቀፍ የህጻናት ጥምረትና የህጻናት ፓርላማ እንዲኖር ይደረጋል፣
 8. ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ህጻናት በቂ እንክብካቤና ድጋፍ የሚያገኙበት አሰራር ይዘረጋል፣ የአዕምሮ ዝግመት ላለባቸው ህጻናት ተገቢ የትምህርት ፕሮግራሞች ይዘጋጃሉ፣
 9. ህጻናት የልደት ምስክር ወረቀትና ሌሎች የወሳኝ ሁነት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወላጆችና ማህበረሰቡ በቂ ትምህርትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችል ስራ ይሰራል፣
 10. ጨቅላ ህጻናት በሚኖሩበት አካባቢ የቅድመ ትምህርት አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር ይዘረጋል፡፡

ለዜጎች የተሟላ ስብዕናና ሁለንተናዊ ደህንነት ኃይማኖት ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በአካልና በስነ-ልቦና የጠነከረ ትውልድ ለመፍጠር ኃይማኖቶች የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ በማህበረሰብ ዕድገትና ደህንነት ላይ የተሰሩ ልዩ ልዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሰረተ፣ ሚዛናዊ የሆነ የቁስ እና መንፈሳዊ ዕድገት ለጤናማ ማህበረሰብ ግንባታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለኃይማኖትና ኃይማኖተኛነት የሚሰጡትን ከፍተኛ ዋጋ እንዲሁም ኃይማኖት በህብረተሰብ ዕድገት ላይ ያለውን በሳይንስ የተረጋገጡ ሀቆች ታሳቢ በማድረግ ነእፓ ኃይማኖትን በተመለከተ የሚከተሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች ይከተላል፡፡

 1. ሁሉም ኃይማኖቶች እኩል ናቸው፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ወይም የአንድን ኃይማኖት ተከታዮች ከሌላው ኃይማኖት ተከታዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊያበላልጡ የሚችሉ አሰራሮች፣ ወጎችና ልማዶች አይኖሩም፣
 2. መንግስትና ኃይማኖት የተለያዩ ይሆናሉ፡፡ መንግስት በኃይማኖት ተቋማት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፣ እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማት በመንግስት ተቋማት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግስትና የሀይማኖት ተቋማት የጋራ በሆኑ አጀንዳዎች ዙሪያ በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ ይችላሉ፣
 3. ማንኛውም ሰው የፈለገውን እምነት የመከተልና የማስፋፋት ነጻነት አለው፣ በኃይማኖት ማስገደድ አይኖርም፣
 4. የአንድ ኃይማኖት ተከታዮች ባሉበት አካባቢ የእምነት ተቋሞቻቸውን የመገንባት ነጻነት አላቸው፣ መንግስት እንደ አስፈላጊነቱ የእምነት ተቋማት የሚገነቡበት ቦታ ሊሰጥ ይችላል፣
 5. የአንድ ዕምነት ተከታዮች በሚበዙበት ክልሎችና አካባቢዎች ለሚኖሩ፣ በቁጥር አናሳ የሌላ እምነት ተከታዮች እምነታቸውን በነጻነት የማራመድ፣ የእምነት ተቋሞቻቸውን የመገንባት፣ የእምነት ተከታዮቻቸውን የማስተማር ወዘተ መብታቸው ይከበራል፣
 6. በእምነቶች መካከል እውነተኛ መቻቻል እንዲኖር፣ የተለያየ እምነት ተከታዮች ተከባብረውና ተቻችለው እንዲኖሩ በእምነቶች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፣
 7. የማናቸውንም እምነት ተከታዮች በእምነታቸው እንዲሸማቀቁና እንዲሰጉ የሚያደርጉ ቢሮክራሲያዊ፣ ህጋዊ፣ የሚዲያና የፖለቲካ ስራዎች አይኖሩም፣
 8. የሁሉም ኃይማኖቶች መሰረታዊ መልዕክት ሰላም፣ ፍቅር፣ ሰብዓዊነትና ወንድማማችነት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህ መሰረት ማንኛውንም ኃይማኖት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሽብርና ፀጥታ መደፍረስ ጋር የሚያገናኝ አመለካከትና አሰራር አይኖርም፣
 9. የኃይማኖት ምሁራንና የኃይማኖት ተቋማት ለሀገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለዘላቂ ልማት መረጋጋጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችል አሰራር ይዘረጋል፡፡
 1. በአካልና በመንፈስ የዳበረ ዜጋን ለመፍጠር ስፖርት ትልቅ ሚና እንዲጫወት ተገቢ የፖሊሲ ትኩረትና ድጋፍ ይደረጋል፣
 2. ዜጎች ለስፖርት ፍቅርና ዝንባሌ እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ ይደረጋሉ፣
 3. ትምህርት ቤቶች የስፖርተኞች መፍለቂያ እንዲሆኑ ለማስቻል በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ በበቂ ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል፣ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊ የስፖርት ቁሳቁሶችና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ አካባቢ እንዲኖራቸው በቂ ድጋፍ ይደረጋል፣
 4. ባህላዊ ስፖርቶች እዲዳብሩና እንዲጠናከሩ ክልላዊና ብሄራዊ ውድድሮች በስፋት እንዲዘጋጁ ይደረጋል፣ የሀገራችን ባህላዊ ስፖርቶች በአፍሪካና በዓለም ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ይደረጋል፣
 5. ስፖርት ከማህበረሰብ ጤና ጋር እንዲያያዝ ከጤናው ሴክተር ጋር በቅንጅት የሚሰራበት አሰራር ይመቻቻል፣
 6. የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እንዲስፋፉና በከተሞች ፕላን ውስጥ ተገቢ ትኩረት እንዲያገኙ ይደረጋል፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በማቋቋም የግሉ ዘርፍ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ድጋፍና ማበረታቻ ይደረጋል፣
 7. ስፖርታዊ ውድድሮች ለሰላም፣ ለአብሮነት፣ ለማህበራዊ መስተጋብር፣ በህዝቦች መካከል የፍቅርና የአንድነት ድልድይ ለመገንባት አስተዋፅዖ ማድረግ እንዲችሉ ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚሰሩበት የአሰራር ማዕቀፍ ይዘጋጃል፣
 8. ስፖርት በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በእኩል እንዲስፋፋ ይደረጋል፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላላቸው አካባቢዎች ድጋፍ ይደረጋል፣
 9. ሀገራችን በዓለም ደረጃ እውቅና ባገኘችባቸው የስፖርት ዓይነቶች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንድትችል ልዩ ድጋፍ ይደረጋል፣
 10. የስፖርት ፌዴሬሽኖች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል አደረጃጃትና ነጻነት እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ ልማት ያለው ጠቀሜታ ዓለም-ዓቀፍ እውቅና እና ድጋፍ እያገኘ መጥቶ በአሁኑ ሰዓት ወሳኝ የፖሊሲ አጀንዳ ሆኗል፡፡ የበረሃማነት መስፋፋት፣ የአካባቢ ብክለት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የደን መመናመን፣ የወንዞችና ሀይቆች የውሀ መጠን መቀነስ ወዘተ በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በመቀነስ ለሰዎች ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ሆኗል፡፡ ለአካባቢ መጎሳቆል በተለይ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገሮች ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት የተበከለ ጭስና ኬሚካል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በታዳጊ ሀገሮችም የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ያለው አነስተኛ ግንዛቤና ደካማ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለችግሩ መስፋት ጉልህ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡

በሀገራችን የአካባቢ ብክለትና የደኖች መመናመን ከጊዜ ወደ ጊዜ ብሄራዊ ስጋት እየሆነ የመጣ ሲሆን የመንግስት ትኩረት ማነስና ዝቅተኛ የህብረተሰብ ግንዛቤ በሀገራችን ካለው አስከፊ ድህነት ጋር ተዳምሮ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ነእፓ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ለሀገር ኢኮኖሚና ሁለንተናዊ ደህንነት ያለውን ከፍተኛ አስፈላጊነት በመረዳት ለአካባቢ ጥበቃና ተያያዥ ለሆኑ አጀንዳዎች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ለተፈጥሮ ሀብትና ለአየር ንብረት መጠበቅ በቂ የፖሊሲ ድጋፍ የሚሰጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በሀገራችን ለመገንባት ነእፓ የሚከተሉትን የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

 1. በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ እንዲቀረጽ ይደረጋል፡፡ ፖሊሲውን ሊያስፈጽም የሚችል ጠንካራ ተቋም በፌደራል መንግስትና በክልል መስተዳድር አካላት ይቋቋማል፣
 2. ዜጎች ከብክለት ነጻና ጤናማ በሆነ አካባቢ መኖር እንዲችሉ ይደረጋል፣ ህብረተሰቡ በአካባቢ እንክብካቤ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያግዙ ስራዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር ይሰራሉ፣
 3. የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የአካባቢ ብክለትን እንዳያስከትል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፣ ከባቢ አየርን የሚበክሉ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል፣
 4. ሰፋፊ እና በህዝብና በመንግስት የሚጠበቁ አረንጓዴ አካባቢዎች እንዲስፋፉ ድጋፍ ይደረጋል፣
 5. አማራጭ የሀይል ምንጮችን በመፍጠር የደን መጨፍጨፍን መቀነስ የሚያስችል የተቀናጀ የአሰራር ስርአት ይዘረጋል፣
 6. ጥቅም ላይ የዋሉ ቁሳቁሶችንና ተረፈ ምርቶችን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂና አሰራር እንዲስፋፋ ድጋፍ ይደረጋል፣
 7. በልዩ ልዩ አካላት የሚገነቡ የልማት ተቋማት ከመገንባታቸው በፊት ከአካባቢያዊና ማህበራዊ አሉታዊ ተጽዕኖ ነጻ መሆናቸው የሚረጋገጥበት የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡